እ.አ.አ በሐምሌ 20-2024 ዓ.ም በኢንዲያናፖሊስ፣ ኢንዲያና  የተካሄደው ብሔራዊ የቅዱስ ቁርባን ኮንግረስ እ.አ.አ በሐምሌ 20-2024 ዓ.ም በኢንዲያናፖሊስ፣ ኢንዲያና የተካሄደው ብሔራዊ የቅዱስ ቁርባን ኮንግረስ 

የር.ሊ.ጳ ልዩ መልእክተኛ እ.አ.አ የ2024 ዓ.ም የሚከበረውን የዓለም የተልዕኮ ቀን ይፋ አደረጉ!

በኢንዲያናፖሊስ፣ ኢንዲያና በተካሄደው 10ኛው ብሔራዊ የቅዱስ ቁርባን ኮንግረስ ጎን ለጎን በተካሄደው ልዩ አቀባበል፣ ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግሌ እና ብፁዕ ካርዲናል ክሪስቶፍ ፒየር እ.አ.አ በጥቅምት 20/2024 ዓ.ም የሚከበረውን የዓለም የተልዕኮ እለተ ሰንበት መደገፍ ያለውን ጠቃሚነት አስምረውበት ከ1,100 በላይ ግዛቶች በመንፈሳዊ አገልግሎት እጥረት ትግል ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

የቫቲካን የስብከተ ወንጌል ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ የወንጌል ስርጭት አገልግሎት ክፍል ዋና ጸኃፊ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግሌ እና በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙት ብፁዕ ካርዲናል ክሪስቶፍ ፒየር በዓለም ዙሪያ ያሉ አማኞችን በእውነት የተቸገሩትን ለመርዳት የሚስዮናዊነት መንፈስ እንዲታደስ ጠይቀዋል።  

በሐምሌ 20 ቀን በኢንዲያናፖሊስ ኢንዲያና በተካሄደው 10ኛው ሀገር አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ላይ ብፁዓን ካርዲናሎች 98ኛውን የዓለም ተልዕኮ እለተ ሰንበት እ.አ.አ በጥቅምት 20/2024 ዓ.ም እንደሚከበር ገልጸው፣ ይህንን ለማስተዋወቅ በዚህ ዓመት በአብዛኞቹ የአሜሪካ አህጉረ ስብከት የሚጠቅሙ ቁሳቁሶችን አቅርበዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዘንድሮው መሪ ቃል "ሂዱና ሁሉንም ሰው ወደ ማዕዱ ጋብዙ" የሚለውን መርጠዋል።

በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው የጳጳሳዊ ተልእኮ ማኅበራት ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ የጳጳሱ ልኡካኖች ዓለማቀፍ የተልዕኮ ቀን እለተ ሰንበት የመሰብሰቢያ ቀን ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኒቱን የስብከተ ወንጌል ቃል ኪዳን ለማደስ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተልዕኮዎችን ለመደገፍ አጋጣሚውን የሚፈጥር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ላይ የቦርድ አባሎቹን የቅዱስ ጳውሎስ እና የሚኒያፖሊስ ሊቀ ጳጳስ በርናርድ ሄብዳ እና የማያሚ ሊቀ ጳጳስ ቶማስ ዌንስኪን ጨምሮ 50 የሚጠጉ ጳጳሳት ከቦርድ አባል ባሪ ጃክሰን ጋር ተገኝተዋል።

የዓለም ተልዕኮ እለተ ሰንበት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ ከአራቱ ጳጳሳዊ ተልእኮ ማኅበራት አንዱ በሆነው የእምነት ማስፋፊያ ማኅበር ተነሳሽነትን በመውሰድ የዓለም ተልእኮ እለተ ሰንበት ቀን በ1926 እ.ኤ.አ. እንዲከበር በወሰኑት መሰረት በቀጣዩ አመት የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ስብስብ መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን እናም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ ዓለም አቀፋዊ የአብሮነት ቀን መከበሩ መጀመሩ ይታወሳል።

በአለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ በጥቅምት ወር የመጨረሻው እሁድ ላይ የሚካሄደው የአለም ተልዕኮ እለተ ሰንበት ለመላው ቤተክርስትያን ከ1,100 በላይ አገረ ስብከቶችን ለመርዳት እና በተለይም በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እና የክርስቶስ መስካሪዎች ለሆኑ ለድሆች ተግባራዊ እርዳታ ለመስጠት የሚደረግ ልዩ ጥረት አካል ነው።

የጸሎት እና የስጦታ ቀን መነሻ የሆነው በ19ኛው ክፍለ ዘመን በፈረንሳይ አገር ሲሆን መእመን የነበሩ ብፅዕት ፓውሊን ያሪኮት ጓደኞቿ በየቀኑ ለተልእኮው እንዲጸልዩ እና በሳምንት አንድ ሳንቲም እንዲሰጡ በጠየቁ ጊዜ ነበር እለቱ የተጠነሰሰው። ያ በመጀመሪያ የተሰበሰበው መባ ወደ ሉዊዚያና ሀገረ ስብከት ተልኳል፣ ከዚያም ከፍሎሪዳ ወደ ካናዳ፣ እንዲሁም ወደ ባርድስታውን፣ ኬንታኪ ተነሳሽነቱ መስፋፋቱ ይታወሳል።

በሰሜን አሜሪካ ውስጥ ያሉ ጳጳሳዊ ተልእኮ ማኅበራት ለሚስዮን ግዛቶች የሰበሰበውን መባ በቀጥታ ያሰራጫሉ።

ጳጳሳዊ ተልእኮ ማኅበራት (TPMS) በሊቀ ጳጳሱ አገልግሎት የሚስዮን እና አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን በጸሎት እና በበጎ አድራጎት ለመደገፍ የተዘረጋ ዓለም አቀፍ ትሥሥር ነው። እነዚህም የእምነት ማስፋፊያ ማኅበር፣ የሐዋርያው ​​የቅዱስ ጴጥሮስ ማኅበር፣ የሚስዮናውያን የልጅነት ማኅበር (ኤም.ሲ.ኤ)፣ እና የካህናትና የሃይማኖት ሚስዮናውያን ማኅበር ያካትታሉ።

በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ጳጳሳዊ ተልእኮ ማኅበራት በእያንዳንዱ አብያተ ክርስቲያናት ፍላጎቶች ላይ ተመስርተው ሀብቶች በፍትሃዊነት እና በእኩልነት እንዲከፋፈሉ በአጥቢያ ጳጳሳት፣ አብያተ ክርስቲያናት እና ሚስዮናውያን ጉባኤዎች በኩል ይሰራሉ።

ገንዘቡ በቀጥታ ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ሚሲዮን ግዛቶች ጳጳሳት ይደርሳል፣ ይህም በሁለቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት እንዲኖር ያስችላል።

ካርዲናል ፒዬር፡ የቤተክርስቲያንን ሚስዮናዊ ገጽታ እንደገና ማንቃት ያስፈልጋል አሉ

የጳጳሳዊ ተልእኮ ማሕበር የቦርድ አባል የነበሩት ካርዲናል ፒየር በንግግራቸው የማህበራቱን አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተው በሰጡት አስተያየት በተለያዩ ሀገራት ውስጥ በንዑስነት ያገለገሉትን የግል ልምዳቸውን አካፍለዋል፣ ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ የጳጳሳዊ ተልእኮ ማሕበር ድጋፍ ተጠቃሚ ሆነዋል ሲሉ ተናግረዋል።

“በዓለም ተልእኮ እለተ ሰንበት ላይ እያዘጋጀን ያለነው ስብስብ ወሳኝ ነው” በማለት አጽንኦት ሰጥተው ሲገልጹ፣ “ይህን የቤተ ክርስቲያን ገጽታ እንደ ሁለንተናዊ ተልእኮ እንደገና ማነቃቃት አለብን፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የመጀመሪያው ሚስዮናዊ በመሆናቸው በእነዚህ ጥረቶች ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መደገፍ አለብን” ሲሉ ተናግረዋል።

ካርዲናል ታግሌ፡ ለመንፈሳዊ ተልዕኮዎች ጸልዩ

ይህ በንዲህ እንዳለ ብፁዕ ካርዲናል ታግሌ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የስብከተ ወንጌል ትምህርት ቤት ጽሕፈት ቤት ሰላምታ ካስተላለፉ በኋላ እነዚህን አስተያየቶች አስተላልፈዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስን ምሥራች ለመካፈል በሚፈልጉ ምእመናን እና ሃይማኖተኛ በሆኑ ሰዎች በተቋቋመው የሚስዮን ማኅበራት መሠረታዊ አመጣጥ ላይ ተመሥርተው አስተያየት የሰጡ ሲሆን "የተልእኮ ማኅበራት ኢየሱስን ለማሳወቅ ባላቸው ጥልቅ መንፈሳዊ ቁርጠኝነት ላይ ነው" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“የተልእኮ ማኅበራት ኢየሱስን ለማስታወቅ ባለው ጥልቅ መንፈሳዊ ቁርጠኝነት ላይ የተመሰረቱ ናቸው” ያሉት ካርዲናል ታግሌ ሚስዮናውያን በእስያ፣ በአፍሪካ፣ በኦሽንያ፣ በአማዞን ክልል እና በላቲን አሜሪካ ሐዋርያዊ ወንጌላውያን ምን እንደሚሠሩ መረጃን በማካፈል በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ያለውን የሚስዮናዊነት መንፈስ ማደስ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ከ1,150 በላይ ግዛቶች

ብፁዕ ካርዲናል ታግሌ በአለም ሚስዮን እለተ ሰንበት ላይ በብዙዎቹ 1,150 ግዛቶች ካጋጠሟቸው ተሞክሮዎች ታሪኮችን አካፍለዋል።

"እስያ በዓለም ላይ በሕዝብ ብዛት ዋነኛ አህጉር ነች። ከዓለም ሕዝብ ውስጥ ሁለት ሦስተኛው በእስያ ውስጥ ነው የሚገኘው፣ ነገር ግን በእስያ ውስጥ ከሚገኙት ሕዝብ መካከል ሦስት በመቶው ብቻ ክርስቲያን ናቸው" በማለት በካምቦዲያ አንድ ምዕመናን ብቻ ያለውን ደብር ሲያስታውሱ እና አምስት ምእመናን ብቻ ያለውን የኔፓል አንድ ቄስ ጋር መገናኘታቸውን አስታውሰዋል።

በአለም ተልዕኮ እለተ ሰንበት ላይ የሚተማመኑ

“ከኤሽያ እና ከአፍሪካ የሚመጡ ጳጳሳት ጥሪዎች ይደርሰኛል፣ እና ብዙ ጊዜ፣ በመጀመሪያዎቹ ሶስት ደቂቃዎች ውስጥ፣ ምንም አይነት ቃል አልሰማም፣ ማልቀስ ብቻ… በአለም ተልዕኮ እሁድ የሚተማመኑ ናቸው” ያሉት ካርዲናል ታግሌ "እነዚህን እውነታዎች እና እነዚህን ታሪኮች ለህዝቦቻችሁ ብታካፍሉ ልባቸው በእሳት እንደሚቃጠል እርግጠኛ ነኝ" ብለዋል።

“እነሱም ምሥራቹን አጥብቀው ለሚፈልጉት ለብዙ ሰዎች ለማካፈል መርዳት እንደሚፈልጉ አውቃለሁ” ሲሉ አክሎም “ከሁሉ የሚበልጠው የምሥራች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ብሏል።

24 July 2024, 11:25