ፓሪስ ላይ የሚካሄዱ የኦሎምፒክ ውድድሮች ፓሪስ ላይ የሚካሄዱ የኦሎምፒክ ውድድሮች  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በፓሪስ የሚካሄዱ የኦሎምፒክ ውድድሮች ስምምነትን እንዲያሳድጉ ተመኙ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድሮ በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ የሚካሄደው የበጋ ጊዜ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከመጀመራቸው አስቀድመው መልዕክት ልከዋል። ቅዱስነታቸው ከኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከውድድሩ ቀደም ብሎ በፓሪስ ለቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ከላኩት ሰላምታ እና ጸሎት ጋር፥ የስፖርት ዝግጅቱ ዓለም በእጅጉ የሚፈልገውን ሰላም እና ወዳጅነትን እንዲያሳድግ ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እግዚአብሔር አብ የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን በማንኛውም መንገድ ለሚሳተፉት በሙሉ ለአትሌቶችም ሆኑ ለተመልካቾች ስጦታዎቹን እንዲያድላቸው፥ እንደዚሁም ዝግጅቱን ለሚያስተናግዱት በተለይም የፓሪስ ከተማ እና የሌሎች አካባቢዎች ምዕመናንን እንዲደግፋቸው እና እንዲባርካቸው በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ቅዱስነታቸው ጸሎቶቸውን እና መልካም ምኞታቸውን የላኩት፥ ዘንድሮ ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 5/2016 ዓ. ም. በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ አስተናጋጅነት የሚካሄዱ የበጋ ጊዜ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በማስመልከት ዓርብ ሐምሌ 12/2016 ዓ. ም. ጠዋት ፓሪስ በሚገኝ በቅድስት ማዴሊን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት እንደሆነ ታውቋል።

በኦሎምፒክ ውድድሮች ወቅት የቀረበ የሰላም ጸሎት
በፓሪስ የሚካሄዱ የዘንድሮው የኦሎምፒክ ውድድሮች የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ዕለትን ምክንያት በማድረግ በቅድስት ማዴሊን ቤተ ክርስቲያን ዓርብ ሐምሌ 12/2016 ዓ. ም. የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴን ያዘጋጁት በፈረንሳይ የካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ የፓሪስ ሀገረ ስብከት እና የውድድሩ አስተባባሪ ቡድን እንደሆኑ ታውቋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድምጽ የተሰጠበት የኦሎምፒክ ውድድሮች የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ውድድሩ ከሚጀምርበት ከሐምሌ 19/2016 አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ የተከናወነ እና ፓራሊምፒክ ውድድር እስከሚጠናቀቅ እስከ ጳጉሜ 3/2016 ዓ. ም. ድረስ እንደሚቆይ ታውቋል።

ዓርብ ሐምሌ 12/2016 ዓ. ም. ጠዋት ፓሪስ ውስጥ በሚገኝ በቅድስት ማዴሊን ቤተ ክርስቲያን የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት የመሩት በፈረንሳይ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ሊቀ ጳጳሳ አቡነ
ሰለስቲኖ ሚሊዮሬ ሲሆኑ፥ ከእርሳቸው ጋርም የፓሪስ ከተማ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሎሬን ኡልሪክ፣ በፈረንሳይ የዲኝ ሀገረ ስብከት ጳጳስ እና በፈረንሳይ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የኦሎምፒክ እና የፓራሊምፒክ ውድድሮች ተወካይ አቡነ ኤማኑኤል ጎቢሊያርድ ጸሎት አሳርገዋል። በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አቶ ቶማስ ባች፣ ዲፕሎማቶች እና ታዋቂ የስፖርት ግለሰቦች ተገኝተዋል።

እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ልብን መክፈት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት መንበር መግለጫ ጽ/ቤት በኩል ለፓሪስ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ለሆኑት አቡነ ኡልሪክ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ዓርብ ማለዳ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ከመስዋዕተ ቅዳሴው ዓላማ ጋር ያላቸውን አንድነት በመግለጽ፣ ለውድድሩ ስኬታማነት በማንኛውም መንገድ የሚተባበሩትን በሙሉ እግዚአብሔር እንዲባርክላቸው በጸሎት ጠይቀው፥ ክርስቲያን ማኅበረሰቦችም የቤተ ክርስቲያኖቻቸውን፣ የትምህርት ቤቶቻቸውን እና የቤታቸውን በሮች በስፋት ከፍተው እንግዶችን እንዲቀበሏቸው አደራ ብለዋል።

በተለይም ልባቸውን እንዲከፍቱ አደራ ብለው፥ ለሁሉም ሰው በሚያደርጉት መልካም አቀባበል፣ ውለታና ልግስና፣ በውስጣቸው ለሚገኝ እና ደስታውን ለሚገልጥላቸው ኢየሱስ ክርስቶስ እየመሰከሩ ለመከራ እና ለችግር የተጋለጡትን ሰዎች ባለመርሳታቸው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህም ባለፈ፥ “ውድድሩ ለመላው የፈረንሳይ ሕዝብ ወንድማማችነትን እንደሚያመጣ፥ ከልዩነቶች እና ቅራኔዎች ይልቅ የሀገሪቱን አንድነት ለማጠናከር የሚያስችል አስደናቂ ዕድል እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

ስፖርታዊ ዓለም አቀፋዊ ቋንቋ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የውድድሩ አዘጋጆች ደስታን በመጋራት፥ “በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ተወዳጅ የሆነውን የስፖርት ውድድር በማዘጋጀት በተለይም ስፖርት ከድንበር፣ ከቋንቋ፣ ከዘር፣ ከብሔር እና ከሃይማኖት በላይ የሆነ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ነው” በማለት አዘጋጆችን አመስግነዋል።

ቅዱስነታቸው “ስፖርት ሰዎችን አንድ የሚያደረግ፣ በመካከላቸውም የጋራ ውይይቶችን እና መግባባትን የሚያሳድግ፣ ራስን ለማሸነፍ የሚያስችል፣ የመስዋዕትነት መንፈስን የሚያጎለብት፣ በእርስ በርስ ግንኙነቶች መካከል ታማኝነትን የሚያጎለብት፣ የራስ ውስንነትን እና የሌሎችን ክብር ለመገንዘብ የሚያስችል ነው” በማለት አስረድተዋል። በማከልም “የኦሎምፒክ ውድድሮች በእውነት ‘ውድድሮች’ መሆናቸውን ከቀጠሉ፣ ሌላው ቀርቶ በጠላትነት ወቅትም ለሕዝቦች ልዩ የመሰብሰቢያ ቦታ ሊሆን ይችላሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

ጓደኝነትን እና አክብሮትን ማዳበር
አምስቱ የተጠላለፉ የኦሎምፒክ ዓርማ ቀለበቶች ስፖርታዊ ውድድሩ ሊገልጽ የሚገባውን የወንድማማችነት መንፈስ እንደሚወክሉ ጠቁመው፣ የዘንድሮው የፓሪስ ኦሊምፒክ ውድድሮች ከሁሉም የዓለም አገራት የሚመጡ ተወዳዳሪዎች እርስ በርስ የሚተዋወቁበት እና አንዱ ሌላውን የሚያደንቅበት፣ ጭፍን ጥላቻ ተውግዶ ንቀት፣ አለመተማመ እና ጥላቻ ባለበት መከባበር እና ወዳጅነት የሚያድግበት አጋጣሚ እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።

ጦርነትን ሳይሆን ሰላምን የሚያበረታቱ ውድድሮች
“የስፖርት ውድድሮች ሰላምን እንጂ ጦርነትን አያበረታቱም” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የስፖርት ትክክለኛ መንፈስ ይህ መሆኑን በማመን፥ በጥንት ጊዜያት የሚደረጉ ስፖርታዊ ውድድሮች መግባባትን በጥበብ እንደሚፈጥሩ እና ይህ ባሕል በዛሬው ዓለምም እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ “የዓለም ሰላም ክፉኛ አደጋ ላይ በወደቀበት በዚህ አስጨናቂ ወቅት፥ ግጭቶችን አስወግዶ ወደ መግባባት ለመድረስ ሁሉም ሰው የእርቅ ስምምነቶችን እንዲያከብር ከልብ እመኛለሁ፥ እግዚአብሔርም ምሕረቱን ይስጠን!” ብለዋል።

"የመሪዎች ህሊና ይብራ!"
“መሪዎች ያለባቸውን ከባድ ሃላፊነት እንዲያውቁት እግዚአብሔር ኅሊናቸውን ያብራላቸው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የሰላም ፈጣሪዎች ጥረታቸው ሁሉ እንዲሳካላቸው በመጸለይ፥ ዘንድሮ በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ለሚካሄዱ የኦሊምፒክ ውድድሮች ስኬታማነት፥ የፓሪስ ከተማ ደጋፊ የሆኑት የቅዱስ ጄኔቪዬቭ እና ቅዱስ ዴኒስ እንዲሁም የፈረንሣይ ጠባቂ የሆነች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ አማላጅነት በመለመን፣ በማንኛውም መንገድ በውድድር ዝግጅቱ ላይ ለተባበሩት እና ውድድሩን ለሚሳተፉት በሙሉ ቡራኬአቸውን በመላክ መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

 

 

20 July 2024, 15:54