ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ካቶሊክ ምዕመናን የዴሞክራሲ ቀውስን ለመፍታት መጠራታቸውን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጣሊያን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ለ50ኛ ጊዜ በተከበረው የማኅበራዊ ሳምንት ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው የሰሜን ጣሊያን ከተማ በሆነች ትሪየስቴ በተዘጋጀው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ ሳምንት ማጠቃለያ ላይ ባሰሙት ንግግር፥ ክርስቲያኖች በዴሞክራሲ ሥርዓት የሚነሱ ችግሮችን በተሳትፎ እና ፖለቲካዊ መፍትሄዎችን በማበርከት እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓመታዊው የጣሊያን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ ሳምንት የመጨረሻ ቀን በሆነው እሑድ ሰኔ 30/2016 ዓ. ም. ወደ ትሪየስቴ ተጉዘው በዴሞክራሲ ሥርዓት ላይ የሚደርሱ ቀውሶችን ለማስወገድ የሚረዱ ሃሳቦችን አካፍለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጣሊያ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች እና ማኅበራት ለተወጣጡ ከ900 በላይ ልዑካን ባስተላለፉት መልዕክት፥ ግለሰቦችን እና ማኅበረሰቦችን ያሳተፈ ዴሞክራሲያዊ ሂደት ሊኖር እንደሚገባ ተማጽነዋል።

ቅዱስነታቸው ለልኡካኑ ባሰሙት ንግግር የመጀመሪያው የጣሊያን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ማህበራዊ ሳምንት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1907 ዓ. ም. መከበሩን እና በኋላም የተዘጋጁ የማኅበራዊ ሳምንት በዓላት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የጣሊያንን ዴሞክራሲያዊ ሂደት ለማበረታታት የረዱ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1988 ዓ. ም. እንደገና የጀመረው ዓመታዊው ዝግጅቱ የቤተ ክርስቲያንን ማኅበራዊ አስተምህሮን መሠረት በማድረግ ለማኅበራዊ ክስተቶች በሙሉ የወንጌል ራዕይ ለማቅረብ መፈለጉን ገልጸዋል። “የዴሞክራሲ ቀውስ የተለያዩ እውነታዎችን እና አገራትን አልፎ እንደሚመጣ ሁሉ፣ የማኅበራዊ ለውጦች አመለካከት በማንኛውም የዓለም ክፍል የሚኖሩትን እና የሚሠሩትን ክርስቲያኖች ኃላፊነት ይጠይቃል” ብለዋል።

በአብሮነት እና በደጋፊነት ላይ የተገነባ ተሳትፎ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የቆሰለ ልብ” በማለት በዲሞክራሲ ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ቀውሶች ገጽታዎችን በማመልከት ባሰሙት ንግግር፥ ሙስና እና ማኅበራዊ መገለል ተስፋፍቶ ስልጣን ሌሎችን ማገልገል በማይችልበት ደረጃ ላይ እንደሚደርስ አስረድተው፥ “ዲሞክራሲ” የሚለው ቃል በቀላሉ ከሕዝብ ፍላጎት እና ምርጫ ጋር የሚገጣጠም ብቻ ሳይሆን፥ ሁሉም ሰው ሃሳቡን እንዲገልጽ እና እንዲሳተፍ ሁኔታዎችን ማመቻቸትን ይጠይቃል" ብለዋል።

ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ ገና በለጋ ዕድሜው መገንባት እንደሚገባ እና በዚህም ዜጎች ከርዕዮተ ዓለም እና ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ ሕዝባዊ ፈተናዎችን እንዲቀበሏቸው፣ ክርስቲያኖች ሰብዓዊ ክብርን በማስጠበቅ በሃይማኖት እና በኅብረተሰብ መካከል ፍሬያማ ውይይት እንዲያደርጉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥሪ አቅርበው፥ የበጎ አድራጎት መርሆዎች ተሳትፎን በማበረታታት ለዲሞክራሲ ሥርዓት እንቅፋት የሆነውን ግዴለሽነት በማስወገድ የዲሞክራሲ ትስስር ለመገንባት ያግዛል ብለዋል።

ወንድማማችነት የጋራ ምኞቶችን ያበረታታል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀጥለውም፥ የዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ግብ “የፈወሰ ልብን” እንደሚመስል ገልጸው፥ “ዙሪያችንን ብንመለከት መንፈስ ቅዱስ በቤተሰብ እና በማኅበረሰብ ሕይወት፣ በምጣኔ ሃብት፣ በቴክኖሎጂ፣ በፖለቲካ እና በኅብረተሰብ መስኮች ሳይቀር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የሚያሳዩ በርካታ ምልክቶችን እናያለን” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም፥ ወንድማማችነት ማኅበራዊ ግንኙነቶች እንዲያብቡ ያደርጋል፣ የጋራ ምኞትንም ይፈጥራል ብለዋል። “ጤናማ የዴሞክራሲ ሥርዓትን መገንባት የወደፊት ህልሞች ማዳበር፣ የግል እና የማኅበረሰብ ተሳትፎን ይጠይቃል” ብለዋል።

ፖለቲካዊ ፍቅር ፖለቲካን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያደርሳል
ካቶሊካዊ ምዕመናን ወደ ዝቅተኛ ወይም ወደ ግላዊ እምነት ውስጥ ሳይመለሱ የዲሞክራሲን ችግሮችን
ቶሎ ብለው መፍታት እንደሚገባ ር ዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አደራ ብለዋል።

“ይህም መደመጥን ብዙ የማይጠይቅ ነገር ግን ከሁሉም በላይ በሕዝባዊ ውይይቶች መካከል ፍትህን እና ሰላምን መሠረት በማድረግ ሃሳቦችን በድፍረት ማቅረብ ያስፈልጋል” ብለዋል። በፖለቲካው ዓለም ውስጥ የክርስቲያኖች ተሳትፎ “ፖለቲካዊ ፍቅር” ወይም “የፖለቲካ በጎ አድራጎት” ገጽታዎች ሊኖረው እንደሚገባ እና ይህም ፖለቲካ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ያስችለዋል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “በዚህ ፍቅር ራሳችንን እናሰልጥን፣ እንደ እግዚአብሔር ሕዝቦች አብረን ሆነን ተሳትፎአችንን ማሳደግን እንማር” በማለት በጣሊያን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ለ50ኛ ጊዜ በተከበረው የማኅበራዊ ሳምንት ማጠቃለያ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት ደምድመዋል።


 

08 July 2024, 17:40