ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ዓለም በኢየሱስ ሳይሆን በተዋረደው የሰው ሕይወት መሸማቀቅ እንደሚገባ ተናገሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጣሊያን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ለ50ኛ ጊዜ በተከበረው የማኅበራዊ ሳምንት መዝጊያ ላይ የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መርተዋል። የሰሜን ጣሊያን ከተማ በሆነች ትሪየስቴ ከተማ እሑድ ሰኔ 30/2016 ዓ. ም. በቀረበው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥እግዚአብሔርን ወደ ጎን በማለት የግል ጥቅምን ላስቀደመው ዓለም “በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የሚገባ የተስፋ እና የአዲስ ፍሬ እምነት ያስፈልገዋል” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጣሊያን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የተከበረውን 50ኛ የማኅበራዊ ሳምንት ምክንያት በማድረግ እሑድ ሰኔ 30/2016 ዓ. ም. በትሪየስቴ ከተማ ባሳረጉት የመዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ ዓለም አሁን ማየት የሚፈልገው የእምነት ውድቀት እንደሆነ አስገንዝበዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው በመሆኑ ምክንያት በገዛ አገሩ ሰዎች መጠላቱን በመናገር አስተንትኖአቸውን የጀመሩት ቅዱስነታቸው፥ “በተራ ሕይወቱ ኢየሱስ የአናጺው የዮሴፍ ልጅ እንደሆነ ብቻ በመመልከት የጥበቡን እና የተዓምራቱን ምንጭ መረዳት አልቻሉም” ብለዋል።

“ጠንካራ እና ኃያሉን እግዚአብሔርን መረዳት የሚቻል እና የሚገርም እንደሆነ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ነገር ግን ደካማ በመሆኑ በመስቀል ላይ የሞተው እና ለሌሎች ሲል ሕይወቱን አሳልፎ የሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስ ለአንዳንዶች የሚያፍሩበት እና የማይመቻቸው አምላክ ሊመስላቸው ይችላል ብለዋል።

የእምነት ቅሌት
ዛሬ ዓለም ማወቅ የሚፈልገው ይህ “የእምነት ቅሌት” ነው” ሲሉ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ለዚህ ዓለም ችግር ደንታ ቢስ ያልሆነ ነገር ግን ከሥጋዊ አካል የመነጨ እና በታሪክ መካከል የሰዎችን ሕይወት የሚነካ አዲስ የተስፋ ዘር የሚሆን እምነት እንደሆነ ተናግረዋል።

እግዚአብሔር ጨለማ በጋረደው የዓለም ማዕዘናት ከድሆች፣ ከተረሱት፣ ከተገለሉት መካከል እንደሚገኝ አጥብቀው ተናግረዋል። ብዙውን ጊዜ በክፉ ሥራዎች፣ በተዋረደው ሕይወት፣ በስደተኞች እና በእስረኞች ችግር ማዘን ሲገባ በጥቃቅን ነገሮች እንሸማቅቃለን ብለዋል።

በዚህ ዓለም ክፋት ማፈር
ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም እንኳን በሌሎች ቢጠላ እና እንዲያውም ተፈርዶበት ለሞት ቢዳረግም ለተልእኮው ታማኝ ሆኖ መቆየቱን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እኛ ክርስቲያኖች በምንገኝበት ማንኛውም ቦታ እና ሁኔታ የእግዚአብሔር መንግሥት ነብያት እና ምስክሮች እንድንሆን ተጠርተናል ብለዋል።

“በኢየሱስ ክርስቶስ ሳንሸማቀቅ የሰው ሕይወት በሚዋረድባቸው፣ በሚቆስልባቸው እና በሚገደልባቸው ሁኔታዎች ሁሉ ማዘን እንደሚገባ ተማጽነው፥ የቅዱስ ወንጌልን ትንቢት ወደ ምርጫችን እና ወደ ሥጋችን ማምጣት ይገባል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሰሜን ጣሊያን ለትሪየስቴ ቤተ ክርስቲያን ባቀረቡት ልዩ ጥሪ፥ የተስፋ ወንጌልን ለማዳረስ ግንባር ቀደም በመሆን፣ በተለይም የሚያጽናናን በመፈለግ ከባልካን አገራት የሚመጡ ችግረኞችን ሁሉ በአካልም ሆነ በመንፈስ ማበረታታት ይገባል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሁሉም ሰው በወንድማማችነት እና በእህትማማችነት በመኖር የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አብ የተወደደ መሆኑን በመገንዘብ በጋራ እንዲሰራ ጥሪ በማቅረብ ቃለ-ምዕዳናቸውን ደምድመዋል።

 

08 July 2024, 17:45