በደቡብ ኢትዮጵያ ጎፋ ዞን በከባድ ዝናብ ምክንያት የተከሰተው የመሬት መንሸራተት በደቡብ ኢትዮጵያ ጎፋ ዞን በከባድ ዝናብ ምክንያት የተከሰተው የመሬት መንሸራተት  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ኢትዮጵያ ውስጥ በመሬት መንሸራተት የተጎዱትን በጸሎታቸው አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በደቡብ ኢትዮጵያ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ሕይወታቸውን ያጡትን፣ ሐዘን እና ጉዳት የደረሰባቸውን በሙሉ በጸሎታቸው አስታውሰው፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ ልዩ የረሃብ እና የሌሎች አደጋዎች መከሰት መቀጠሉን ገልጸዋል። ጦርነት ምንጊዜም ሽንፈትን የሚያስከትል እንደሆነ ቅዱስነታቸው አስታውሰው፥ የጦር መሣሪያ ምርት እና ሽያጭ የሰው ልጆች መከራን እንደሚያባብስ ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው እንዲሁም እሑድ ሐምሌ 21/2016 ዓ. ም. ተከብሮ የዋለውን ዓለም አቀፍ የአያቶች እና አረጋውያን ቀን በማስታወስ ሁሉም ሰው ዘወትር በጸሎት እንዲያስታውሷቸው እና እንዲደግፏቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ሐምሌ 21/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ያቀረቡትን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ሲያጠቃልሉ ባሰሙት ንግግር፥ በደቡብ ኢትዮጵያ በደረሰው ከፍተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ የተጎዱ ወገኖችን በጸሎታቸው አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በአደጋ ምክንያት ስቃይ ከደረሰባቸው እና ዕርዳታን በማድረግ ላይ ከሚገኙት ወገኖች ጎን መሆናቸውን ገልጸዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ጎፋ ዞን በተከሰቱት ሁለት ከባድ የመሬት መንሸራተቶች ከ 257 ሰዎች በላይ መሞታቸው እና ይህ ቁጥር አሁንም እየጨመረ እንደሚገኝ እንዲሁም ለተጎጂዎቹ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ታውቋል። በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ተራራማ አካባቢ የመጀመርያው የመሬት መንሸራተት የተከሰተው ሐምሌ 14 እና 15/2016 ዓ. ም. በጣለው ከባድ ዝናብ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሰዎችን ለማዳን በተሰበሰቡት ሰዎች ላይ እንደነበር ይታወሳል።

ጦርነት ሁሌም ሽንፈትን ያስከትላል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለም ዙሪያ በርካታ ሰዎች በአደጋ እና በረሃብ እየተሰቃዩ እንደሚገኙ ጠቁመው፥ የጦር መሣሪያ ምርት እና ሽያጭ እንደቀጠለ እና ይህም ትላልቅ እና ትናንሽ ጦርነቶችን በማቀጣጠል የሰውን ሕይወት እያጠፋ፣ ንብረትን እያወደመ እንደሚገኝ እና ድርጊቱም “አሳፈሪ!” በመሆኑ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መታገስ እንደሌለበት ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር በማያያዝ ድርጊቱ በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ የተከፈተውን የኦሎምፒክ ውድድሮች የወንድማማችነት መንፈስ የሚጻረር ነው” ብለው፥ “ጦርነት ዘወትር ለሰው ልጅ ሽንፈት ነው” ሲሉ አስምሮበታል።

አያቶችን እና አረጋውያንን ማስታወስ ይገባል!
እሑድ ሐምሌ 21/2016 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን የሚከበርበት ዕለት መሆኑን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ለዘንድሮው ዓለም አቀፍ የአያቶች እና አረጋውያን ቀን የመረጡት መሪ ጥቅስ ከመዝ. 71፡9 ላይ የተወሰደ እና “በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፥ ጕልበቴም ባለቀ ጊዜ አትተወኝ” የሚል እንደሆነ ይታወሳል።

አረጋውያንን ብቻቸውን መተው አሳዛኝ እውነታ እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ ‘አትተወኝ!’ እያለ የሚወተውት የአረጋዊ ድምፅ ተደማጭነትን ሊኖረው ይገባል ብለዋል። የወደፊት ሕይወታችን የሚመካው አያቶች እና የልጅ ልጆች አብረው የሚኖሩበትን መንገድ ሲማሩ እንደሆነ በመግለጽ፥ በንግግራቸው ማጠቃለያም ሁሉም ሰው አረጋውያንን ዘወትር እንዲያስታውስ እና እንዲደግፍ አደራ ብለዋል።

 

29 July 2024, 17:29