“አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ወይም ሰው ሠራሽ አስተውሎት “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ወይም ሰው ሠራሽ አስተውሎት  (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ከመሣሪያ ትጥቅ ጋር በተያያዘ ‘ገዳይ’ የሚባሉ መሣሪያዎችን በድጋሚ ማጤን ይገባል አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአቶሚክ የጦር መሣሪያ በተሰቃየች የጃፓኗ ከተማ ሂሮሺማ ውስጥ “የሰው ሠራሽ አስተውሎት ምግባር ለሰላም” በሚል ርዕሥ የተካሄደ የሰላም ጉባኤ ተምሳሌታዊ ጠቀሜታ አጽንኦት በመስጠት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ከተለያዩ የዓለም አገራት የተውጣጡ የሃይማኖት መሪዎች ጃፓን ሂሮሺማ ከተማ ውስጥ “የሰው ሠራሽ አስተውሎት ምግባር ለሰላም” በሚል ርዕሥ ላይ ከሐምሌ 2-3/2016 ዓ. ም. ድረስ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለስብሰባው ተካፋዮች ባስተላለፉት መልዕክት፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በንሐሴ ወር 1945 ዓ. ም. የተጸመው ጥቃት ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋት እንደነበር አስታውሰው፥ ዛሬ በዚያች ከተማ “የሰው ሠራሽ አዕምሮ ምግባር ለሰላም” በሚል ርዕሥ የተካሄደው ስብሰባ “ትልቅ ምሳሌያዊ ጠቀሜታ አለው” ሲሉ ተናግረዋል።

ሰው ሠራሽ አዕምሮ (AI) እና ሰላም
“አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ወይም ሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ሰላም የሚሉት ሁለት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ጉዳዮች ናቸው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በኤኮኖሚ የበለጸጉት የG7 የፖለቲካ መሪዎች ጉዳዩን አስመልክተው ጣሊያን ውስጥ በፑሊያ ግዛት ባደረጉት ስብሰባ ላይ ያቀረቡትን የቅርብ ጊዜ አቤቱታ አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለስብሰባው ተካፋዮች ባስተላለፉት መልዕክት፥ በማሽን ከመታመን ይልቅ ውሳኔዎችን በሰው እጅ በማድረግ አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥተው፥ ማሽን ንም ጊዜም በጥሩ ሁኔታ በተቀመጡለት መስፈርቶች ወይም ስታቲስቲካዊ ግምቶች ላይ በመመሥረት ከብዙ አማራጮች መካከል ቴክኒካዊ ምርጫን እንደሚያደርግ እና የሰው ልጅ ግን መምረጥ ብቻ ሳይሆን በልቡም የመወሰን ችሎታ አለው ብለዋል።

እውነተኛ ውሳኔዎች
እውነተኛ ውሳኔዎች የሰውን ጥበብ እና ግምገማ የሚሹ፥ ነገር ግን በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ ከመጠን በላይ መታመን የሰውን ክብር ሊጎዳ ይችላል ብለዋል። ይህ በትክክል በሂሮሺማ ያየነው እና ዛሬም እያየነው ያለነው ነው ብለው፥ በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ላይ ጦርነትን እና ጥላቻን ጨምሮ የበለጠ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩት መካከል ቴክኖሎጂ መኖሩን እንሰማለን” ሲሉ አክለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም፥ “እንደ ወንድም እና እህት አንድ ላይ በመሆን፣ ከጦር መሣሪያ ትጥቅ ጋር በተያያዘ ከሚደርስ አደጋ አንፃር ‘ገዳይ’ እየተባለ የሚጠራውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት መሣሪያ እንደገና ማጤን አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል። ራስ ገዝ የጦር መሣሪያዎች እና በመጨረሻም አጠቃቀማቸውን መከልከል እንደሚገባ ቅዱስነታቸው አሳስበው፥ በመንበረ ጵጵስናቸው ወቅት ካቀረቧቸው ተማጽኖዎች እና ጥሪዎች ጋር፥ “የትኛውም ማሽን የሰውን ልጅ ሕይወት በከንቱ ማጥፋት የለበትም” በማለት ተማጽኖአቸውን በድጋሚ አቅርበዋል።

ፍትሃዊ ደንብ እንዲዘጋጅ የሁሉ አስተዋፅዖ ያስፈልጋል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ በፊታችን ያሉትን ጉዳዮች ውስብስብነት ስንመለከት፥ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ቁጥጥር “በሕዝቦች እና ሃይማኖቶች ባሕላዊ ሃብቶች ውስጥ ያበረከቷቸውን አስተዋፅዖዎች እንገነዘባለን” ሲሉ ተናግረው፥ ይህም “ቴክኖሎጂያዊ ፈጠራን በጥበብ ለማስተዳደር ለሚሰጡት ቁርጠኝነት ስኬት ቁልፍ ነው” ሲሉ ተማጽነዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም፥ “እያንዳንዳችን ለዓለም የሰላም መሣሪያ እንድንሆን” በማለት ጸሎት ካማቅረባቸው በፊት፥ ስብሰባው ወንድማማችነትን እና ትብብርን የሚያስገኝ ፍሬን እንደሚያፈራ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
 

10 July 2024, 16:23