ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ገዳማውያት ጥሪ እንዲያብብ መጸለይ እንደሚገባ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማኅበራቸው ጠቅላላ እና አውራጃዊ ስብሰባ ለመካፈል ወደ ሮም ከመጡ የስድስት ማኅበራት ገዳማውያት ጋር ሰኞ ሐምሌ 8/2016 ዓ. ም. ጠዋት በቫቲካን ተገናኝተዋል።
ቅዱስነታቸው እንግዶቹን ባገኟቸው ጊዜ ባቀረቡላቸው ጥያቄ ምን ያህል ጀማሪ ተከታዮች እንዳሏቸው ጥይቀው፣ ማኅበሮቻቸው ተከታዮች ከሌሏቸው ወደ ፊት ሊመነምኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቀው፥ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡት አገልግሎት እንዳይቋረጥ ተከታዮች ሊኖሯቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም፥ የገዳማውያት እና ገዳማውያን መንፈሳዊ ሕይወት ሁለት ገጽታዎች ጠቅሰው እነርሱም የሕይወቱ ውበት እና ትሕትና እንደሆኑ ገልጸዋል።
የእግዚአብሔር የጸጋ እና የውበት መልክ
እያንዳንዱ የገዳም ሕይወት ታሪክ በውስጡ የእግዚአብሔር ጸጋ እና ውበት በብርሃን የሚገለጥበት እንደሆነም ቅዱስነታቸው አስረድተው፥ ይህን ውበት ተገንዝበው መሥራቾቻቸው በጊዜው በነበሩ ተጨባጭ ሁኔታዎች መካከል የኢየሱስ ክርስቶስን ውበት የፈለጉበትን እና ያስፋፉበትን መንገድ በመከተል ዘመኑ በሚፈልጋቸው የተለያዩ መንገዶች ምስክርነት እንዲሰጡ አደራ ብለዋል።
ቅዱስነታቸው በማከልም ገዳማውያቱ “መሥራቾቻቸው እንዳደረጉት ሁሉ በዛሬው ዓለም ተጨባጭ ሁኔታዎች መካከል የኢየሱስ ክርስቶስን ውበት መፈለግ እና ማስፋፋት የእያንዳንዱ የማኅበሩ አባል ሃላፊነት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
በትኅትና አስፈላጊ የሆነውን መምረጥ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስክሶስ ለገዳማውያቱ የሚያስተላልፉትን መልዕክት በመቀጠል፥ የልዩ ልዩ ገዳማት መስራቾች ገዳሞቻቸውን የሚጠቅም ነገር ብቻ እንደመረጡ እና ከመጠን በላይ የሆነውን ነገር እንዳልተቀበሉ ገልጸው፥ በዚህም መንገድ በቅዱስ ወንጌል ውስጥ በሚበራው የእግዚአብሔር ፍቅር ራሳቸውን ዕለት በዕለት ማነጻቸውን አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ገዳማውያቱ በስብሰባቸው ወቅት ትህትናን ከእግዚአብሔር ዘንድ በስጦታ ለመቀበል መለመን እንደሚገባ አሳስበው፥ ጉባኤያቸውን በትኩረት እንዳይሳተፉ እና እንዳይስማሙ እንቅፋት የሚሆኑ ማናቸውንም ነገሮች ከራሳቸው እንዲያስወግዱ ጥሪ አቅርበዋል። ይህን በማድረጋቸው ወቅቱ የሚፈልገውን በመረዳት ለወደፊቱ ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ" እንደሚችሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተናግረዋል።
“ታላቅ ተልዕኮ ነው!”
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም ገዳማውያቱ እና የድህነት ሕይወት በታዛዥነት ለመኖር ያላቸውን ቁርጠኝነት በማጉላት፥ “ይህም በእግዚአብሔር አብ የተሰጣቸውን ታላቅ ተልዕኮ እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል” ብለዋል።
የጸሎትን አስፈላጊነት በተለይም በመንበረ ታቦት ላይ በሚገኝ ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ቀርቦ የመጸለይ አስፈላጊነትን አስታውሰው፥ ከልብ የሚመነጭ ጸሎት በእግዚአብሔር ጎዳና ወደፊት ለመጓዝ እንደሚረዳ አስረድተዋል።
“ጥሪ እንዲያብብ መጸለይ ያስፈልጋል!”
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ለተቀበሏቸው የስድስት ገዳማት ተወካዮች ያቀረቡትን መልዕክት ከማጠቃለላቸው በፊት በተናገሯቸው የምስጋና እና የማበረታቻ ቃላት፥ ገዳማውያቱ አገልግሎታቸው ሳይቋረጥ እንዲቀጥል የሚያደርጉ ተከታዮችን ለማፍራት መጸለይ እንደሚገባ አሳስበው፥“በጎነታችሁን ወደፊት የሚያራምዱ ተተኪዎች እንዲኖሯችሁ ያስፈልጋል” ሲሉ ተናግረው፥ ለዚህም መጸለይ እንደሚገባ እንዲሁም ለዝግጅቱም ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ እና ጥረቱም መልካም እንዲሆን ክትትል ሊደረግለት ይገባል ብለዋል።