ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በትሪየስቴ ከተማ ያቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በትሪየስቴ ከተማ ያቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቁርጠኝነት ለሰላም መሥራት እና መጸለይ እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰሜን ምሥራቅ ጣሊያን ከተማ ትሪየስቴ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ማጠቃለያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ በተለይ ዩክሬን፣ ፍልስጤምን፣ እስራኤል፣ ሱዳንን ምናማርን እና በጦርነት ምክንያት የሚሰቃዩ ሌሎች የዓለማችን ክፍሎች በማስታወስ ለሰላም መጸለይ እንደሚገባ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በትሪየስቴ ከተማ እሑድ ሰኔ 30/2016 ዓ. ም. ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ማጠቃለያ ላይ፥ ሁሉም ሰው ለዓለም ሰላም በኅብረት ለመጸለይ እና ለመሥራት የገባውን ቃል እንዲያድስ ጥሪ አቅርበዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥሪያቸውን ያቀረቡት እሑድ በሰሜን ምሥራቅ የጣሊያን ከተማ ትሪየስቴ ያቀረቡትን የእኩለ ቀን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከመምራታቸው አስቀድመው ነበር።

“ከዚች ከተማ ሆነን ለሰላም ለመጸለይ እና በጋራ ለመሥራት የገባነውን ቃላችንን እናድስ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ለዩክሬን፣ ለፍልስጤም፣ ለእስራኤል፣ ለሱዳን፣ ለምያንማር እና በጦርነት ምክንያት ለሚሰቃዩ ሰዎች ሁሉ፥ በሞንቴ ግሪሳ ተከብራ ለዋለች የሰላም እናት እና ንግሥት ለሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ጸሎታችንን እናቅርብ ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጣሊያን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ለ50ኛ ጊዜ የተከበረው የማኅበራዊ ሳምንት ዝግጅቶችን ላስተባበሩት እና የመስዋዕተ ቅዳሴውን ጸሎት ለተካፈሉት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ከመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ቀደም ብለው የጎበኟቸውን በርካታ ሕሙማንን፣ ታራሚዎችን፣ ስደተኞችን እና ተስፋውቻቸውንም በማሰብ በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው አረጋግጠውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የትሪየስቴ ከተማ ጳጳስ አቡነ ኤንሪኮ ትሬቪሲ በቅርቡ የረዷቸውን ሕሙማን በስም በመጥቀስ ማስታወሳቸው እና ማወቃቸው ሰብዓዊ ክብራቸውን እንደሚያጎላ በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ጦርነትን እና ድህነትን ሸሽተው ለመጡት ብዙ የሌሎች አገራት ሕዝቦች ላደረጉት አቀባበል የትሪየስቴ ነዋሪዎችን አመስግነዋል።

በተለይም ጣሊያን ውስጥ በመካከለኛው አውሮፓ እና በባልካን አገራት መካከል ዋና መዳረሻ እና መስቀለኛ መንገድ የሆነች የትሪየስቴ ከተማ የተለያዩ ሰዎችን በእንግድነት ተቀብላ የማስተናገድ ልዩ የአገልግሎት ጥሪ እንዳላት ጠቁመዋል።

የትሪየስቴ ከተማ ሕዝብ የስደተኞችን ማንነት የማክበር፣ ክፍት መሆን፣ መረጋጋት እና እንግዶችን የመቀበል ሚናን እና የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችንም ቅዱስነታቸው ተገንዝበው፥ ነገር ግን ለምእመናን ትርጉም እና ተስፋ የሚሰጥ የወንጌል ብርሃን በመሆኑ፥ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት በማክበር ሁሉም ሰው በዚህ መንገድ እንዲጸና ብርታትን ተመኝተው ይህም ለዲሞክራሲያዊ መንገድ አስተማማኝ አቅጣጫ አመላካች መሆኑን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰሜን ምሥራቅ ጣሊያን ከተማ በሆነች ትሪየስቴ ያስተላለፉትን መልዕክት ሲደመድሙ፥ የትሪየስቴ ከተማ ሕዝብ በሰብዓዊ ክብር ላይ ምንም ሳይደራደር እና ሳይፈራ በሰዎች እና በክርስቲያናዊ እሴቶች ውስጥ ያለውን ግልፅ እና ጽኑ አቋም በመጠበቅ ወደ ፊት እንዲጓዝ አደራ ብለዋል።

 

 

08 July 2024, 17:51