ፈልግ

ር.ሊ.ጳ. ፍራንችስኮስ “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም” የሚለውን በእርግጠኝነት ይዘን ጉዟችንን እንቀጥል አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሠረት ቅዱስነታቸው በነሐሴ 1/2016 ዓ.ም ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ "ድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አማካኘነት" ኢየሱስን እንዴት እንደፀነሰች እና ብርሃን የሆነ ልጅ ስለመውለዷ” የምያመልክት አስተምህሮ ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም” የሚለውን የሚያጽናኛ እርግጠኝነት ይዘን ጉዟችንን እንቀጥል ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በሚገባ ለመከታተል ያስችላችሁ ዘንድ በእለቱ የተንበበውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፣ ተከታተሉን።

“መልአኩም እንዲህ አላት፤ “ማርያም ሆይ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆ፤ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። ማርያምም መልአኩን፣ “እኔ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፤ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኀይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ የሚወለደው ቅዱሱ ሕፃን፣ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል” (ሉቃስ 1፡30-31፣34-35)።

 

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ወደ ሁለተኛው የድነት ታሪክ ምዕራፍ እንገባለን። መንፈስ ቅዱስ በዘፍጥረት ታሪክ ውስጥ የፈጸመውን ሥራ ካሰላሰልን በኋላ ለጥቂት ሳምንታት ደግሞ ኢየሱስ እኛን በመበዤት ተግባር ውስጥ ባደርገው ሥራ ላይ እናሰላስላለን። ስለዚህ ወደ አዲስ ኪዳን እንሸጋገራለን ማለት ነው። የዛሬው ጭብጥ መንፈስ ቅዱስ በቃሉ መገለጥ ውስጥ ነው የሚለው ይሆናል። በሉቃስ ወንጌል ውስጥ፣ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፣ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል” (ሉቃስ1፡35) የሚለውን እናነባለን።

መንፈስ ቅዱስ እና ቃል ምስጢረ ሥጋዌ

ወንጌላዊው ማቴዎስ ማርያምንና መንፈስ ቅዱስን በሚመለከት ይህን መሠረታዊ ሐቅ አረጋግጦ፣ ማርያም “በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች” (ማቴ 1፡18) በማለት ተናግሯል። ቤተክርስቲያን ይህንን የተገለጠ እውነታ ወሰደች እና ብዙም ሳይቆይ በእምነቷ ምልክት ልብ ላይ አስቀመጠችው። በቁስጥንጥንያ ኢኩሜኒካል (ክርስቲያናዊ) ጉባኤ በ381 ዓ.ም - የመንፈስ ቅዱስን መለኮትነት የሚገልጸው - ይህ አንቀጽ ወደ "የጸሎተ ሃይማኖት መግለጫ" ቀመር ውስጥ ይገባል፣ እሱም በእርግጥ ኒሴን-ቁስጥንጥንያ እየተባለ የሚጠራ ሲሆን በእያንዳንዱ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የምንደግመው ነው። የእግዚአብሔር ልጅ "በመንፈስ ቅዱስ ከድንግል ማርያም ሥጋ ለብሶ ሰው የሆነ" መሆኑን ያረጋግጣል። ስለዚህ ሁሉም ክርስቲያኖች ያንኑ የእምነት ምልክት በአንድነት ስለሚያምኑ ይህ ሁለንተናዊ የእምነት እውነታ ነው። የካቶሊክ አምልኮ ከጥንት ጀምሮ ከዕለት ተዕለት ጸሎቶቹ አንዱን የሆነውን የእግዚአብሔር መልአክ ማርያምን ያበሰረበትን ጸሎት ወስዷል። ሦስቱን ሙገሳዎች አንድ ላይ ብንደግማቸው ጥሩ ነው።

ይህ የብሥራተ ገብርኤል ጸሎት ...

የእግዚአብሔር መልአክ ማርያምን አበሠራት እስዋም በመንፈስ ቅዱስ ፀነሰች – 

እነሆኝ የእግዚአብሔር አገልጋይ እንዳልከኝ ይሁንልኝ

ቃል ሥጋ ሆነ፣ በኛም አደረ …

የቤተክርስቲያን ምሳሌ የሆነች ቅድስት ድንግል ማርያም

ይህ የእምነት አንቀጽ ማርያምን የቤተክርስቲያኗ ምሳሌ የሆነችውን ዋናዋ ሙሽሪት መሆኗን እንድንናገር የሚያስችለን መሰረት ነው። በእርግጥ ኢየሱስ፣ ታላቁ ቅዱስ ሊዮ እንደጻፈው፣ “ልክ በመንፈስ ቅዱስ ከድንግል እናት እንደ ተወለደ፣ እንዲሁ ቤተክርስቲያንን፣ እድፍ የሌለባትን ሙሽራ፣ ሕይወት ሰጪ በሆነው መንፈስ እስትንፋስ ፍሬያማ ያደርጋታል። ይህ ትይዩነት በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሉመን ጄንሲውም (መለኮታዊ መገለጽ) የተሰኘው ሰነድ ውስጥ እንዲህ ይላል፡- “በእሷ እምነትና ታዛዥነት [ማርያም] የአብ ልጅ በምድር ላይ ተወለደ፣ ይህም የተፈጸመው የጥንት ጠላታችን በነበረው በእባቡ ቃል ሳይሆን፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር መልእክተኛ አማካይነት ነው… በእርግጥ ቤተክርስቲያን የተደበቀውን ቅድስናዋን እያሰላሰለች፣ ልግስናዋን እና ታማኝነቷን በመላበስ እና የአብን ፈቃድ በታማኝነት በመፈጸም፣ የእግዚአብሔርን ቃል በእምነት በመቀበል እራሷ እናት ትሆናለች። በስብከቷም በጥምቀት የተወለዱላት ከመንፈስ ቅዱስም ተምረው ከእግዚአብሔርም የተወለዱትን ልጆች ወደ አዲስና ወደማይጠፋ ሕይወት ትመራለች” (ቊ. 63-64) ይላል።

ለእግዚአብሔር የሚሳነው ምንም ነገር የለም  

“መፀነስ” እና “መውለድ” በሚሉት ግሦች ላይ በቅዱሳት መጻሕፍት ጽናት በተጠቆመው ለሕይወታችን በተግባራዊ ነጸብራቅ እንደመደም። "እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች" የተሰኘውን በትንቢተ ኢሳይያስ (7፡14) እናነባለን፡ መልአኩም ለማርያም፡ "እነሆም ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ" (ሉቃ. 1፡31) የሚለውንም በቅዱስ ወንጌል ውስጥ እናነባለን። ማርያም በመጀመሪያ ፀነሰች፣ ከዚያም ኢየሱስን ወለደች፡ በመጀመሪያ በራሷ፣ በልቧና በስጋዋ ተቀበለችው፣ ከዚያም ወለደችው። ይህ ለቤተክርስቲያኗም እንዲሁ ይሆናል፡ በመጀመሪያ የእግዚአብሔርን ቃል ተቀበለችው፣ “በገርነት እንዲነግራት” (ሆሴዕ 2፡14) እና “ሆዷን እንዲሞላ” (ሕዝ. 3፡3)፣ በሁለት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አገላለጾች መሠረት ከዚያም በሕይወቷና በስብከቷ ወለደችው።  

“ባል የለኝምና ይህ እንዴት ይሆናል?” ብላ ለጠየቀችው ማርያም መልአኩ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይወርዳል” (ሉቃስ 1፡34-35) በማለት መለሰላት። ቤተክርስቲያኗም ከጥንካሬዋ በላይ የሆኑ ስራዎች ሲገጥሟት ወዲያው ተመሳሳይ ጥያቄ ትጠይቃለች፡ “ይህ እንዴት ይቻላል?” በዚህ ዓለም ውስጥ ደህንነትን ብቻ የሚፈልግ ለሚመስለው ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስንና ማዳኑን እንዴት ማወጅ ይቻላል? መልሱም እንደዚያው ነው፡- “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፤ ምስክሮቼም ትሆናላችሁ” (ሐዋ. 1፡8) በማለት ከሙታን የተነሣው ኢየሱስ ለሐዋርያቶች እንደ ተናገረው በብሥራተ ገብርኤል ወቅት እነዚህ ለማርያም የተነገሩ ቃላት ናቸው።

ስለ ቤተክርስቲያን በአጠቃላይ የተነገረው ለእያንዳንዱ የተጠመቀ ሰው ይሠራል። ሁላችንም አንዳንድ ጊዜ እራሳችንን፣ በህይወት ውስጥ፣ ከአቅማችን በላይ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እናገኛለን፣ እና እራሳችንን እንጠይቃለን፥ "ይህን ሁኔታ እንዴት መቋቋም እችላለሁ?" እንደዚህ ባሉ አጋጣሚዎች መልአኩ ድንግልን ተሰናብቶ ከመሄዱ በፊት “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም” (ሉቃስ 1፡37) በማለት የተናገረውን ቃላት ለራሳችን ማስታወስ እና መድገም ጠቃሚ ይሆናል ማለት ነው።

እንግዲያውስ ሁል ጊዜም “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም” የሚለውን የሚያጽናኛ እርግጠኝነት ይዘን ጉዟችንን እንቀጥል።

07 August 2024, 11:26

በቅርብ ጊዜ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የተደረገው ግንኙነት

ሁሉንም ያንብቡ >