የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የበጎ አድራጎት ድርጅት ለሊባኖስ ተረጂዎች ዕርዳታን በማድረስ ላይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የበጎ አድራጎት ድርጅት ለሊባኖስ ተረጂዎች ዕርዳታን በማድረስ ላይ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለአደጋ የተጋለጡ የዕርዳታ ሠራተኞችን በጸሎት እንድናስታውሳቸው ጠየቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ሠራተኞች ቀንን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ሕይወታቸውን ለአደጋ በማጋለጥ ወንድማማችነትን የሚመሰክሩ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞችን በጸሎታችን እንድናስታውሳቸው አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰብዓዊነት ቀንን “WHD” ባከበረበት ነሐሴ 13/2016 ዓ. ም. ባስተላለፉት መልዕክት፥ ሁሉም ሰው የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞችን፣ በተለይ በጦርነት እና በአደጋ የተጎዱን ሰዎች ሲረዱ የሞቱትን ወይም የተጎዱትን በጸሎት እንድናስታውሳቸው አሳስበዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት የተሰማሩትን፣ የሞቱትን ወይም የተጎዱትን ለመዘከር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 2008 ዓ. ም. ጀምሮ ዓለም አቀፍ ቀንን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።


ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዕለቱ በተከበረበት ሰኞ ነሐሴ 13/2016 ዓ. ም. በኤክስ ገጻቸው በኩል በስተላለፉት መልዕክት፥ “የሰብዓዊ ዕርዳታ ሰጪዎች የተቸገሩትን በመንከባከብ ሁላችንም ወንድማማቾች መሆን እንደምንችል ያሳያሉ” ብለዋል።

2024፥ ለሰብዓዊ የዕርዳታ ሠራተኞች አደገኛ ዓመት ነበር
በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በጦር መሣሪያ የሚታገዝ ግጭቶች በመጨመራቸው ምክንያት የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች ሞትም በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተመልክቷል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2024 ዓ. ም. የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች በተለይም በአገራቸው ውስጥ ለሚኖሩ የዕርዳታ ሠራተኞች አደገኛ ዓመት ሊሆን እንደሚችል እና በተጠቀሰው ዓመትም 192 የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች ሲገደሉ ከነዚህም ውስጥ 119 ቱ በትውልድ አገራቸው የሚገኙ ሠራተኞች መሆናቸው ታውቋል።

በጋዛ ከፍተኛ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች ሞት ተመዝግቧል
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የበጎ አድራጎት ድርጅት “ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ” እንዳስታወቀው፥ በጋዛ ውስጥ የተገደሉት የዕርዳታ ሠራተኞች ቁጥር የጨመረው የሃማስ ታጣቂዎች በደቡባዊ የእስራኤል ድንበር አካባቢ መስከረም 26/2016 ዓ. ም. ያካሄደውን ጥቃት ተከትሎ እንደሆነ፥ ባለፉት 10 ወራት ውስጥ በድምሩ ቢያንስ 274 የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች መገደላቸውን ገልጿል።

በጋዛ ሰርጥ ባለፉት 10 ወራት ውስጥ የተገደሉት የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች ቁጥር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2021 እና 2022 መካከል በዓለም ዙሪያ ከተደገደሉት የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች አጠቃላይ ቁጥር እንደሚበልጥ ታውቋል።

“ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ” አክሎም የእስራኤል ጦር በጥቅምት ወር በጋዛ ሰርጥ በሚገኝ በቅዱስ ፖርፊዮስ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ባደረሰው ጥቃት ሁለት ብሔራዊ የዕርዳታ ሠራተኞቹ፥ የላቦራቶሪ ቴክኒሻን ቪዮላ ከባለቤቷ እና ከጨቅላ ሴት ልጇ ጋር በአሳዛኝ ሁኔታ መገደላቸውን ገልጾ፥ ሌላ የ35 ዓመቱ አባት ከሁለት ወንድ ልጆቹ ጋር መገደሉን አስታውቋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከጥቅምት ወር 2023 ዓ. ም. ጀምሮ የእስራኤል ጦር ጋዛ ውስጥ በሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች እና በመኖሪያቸው ላይ ቢያንስ ስምንት ጥቃቶችን መፈጸሙን የካሪታስ ቤልጂየም የዓለም አቀፍ ትብብር እና የሰብዓዊ ዕርዳታ ዳይሬክተር አቶ ዣን ኢቭ ቴርሊንደን አስታውሰው፥ እነዚህ አደጋዎች በአጋጣሚ የተከሰቱ አለመሆናቸውንም አስረድተዋል። ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ እንደገለጸው፥ ይህ ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ በሰብዓዊ የዕርዳታ ሠራተኞች ላይ የሞት አደጋ ሊባባስ የቻለው ቅድሚያ የሚሰጥባቸው የፖለቲካ ጉዳዮች እየተጠናከሩ በመምጣታቸው እንደሆነ አስረድተዋል።

በሰላማዊ ሰዎች እና በሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች ላይ ለሚደርሰው አሳዛኝ ሞት ዋናው ምክንያት የአውሮፓ ኅብረት እና አሜሪካ መንግሥት ለእስራኤል ቦምቦችን እና ሌሎች የቁሳቁስ ድጋፍን ጨምሮ ወታደራዊ ድጋፎችን በቀጣይነት በመስጠታቸው መሆኑን ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ ጠቁሟል።

ምንም እንኳን አሜሪካ እና ሁሉም የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት የጦር መሣሪያ ወደ ውጭ የሚላክበትን ሁኔታ እንዲከታተሉ እና አሁን ያለውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ እንዲያከብሩ ወይም ለሰብዓዊ መብት ረገጣ እንዳይውሉ የሚያስገድደውን የተባበሩት መንግሥታት የጦር መሣሪያ ንግድ ስምምነት (ATT) ቢፈርሙም ስምምነቱን ሳያከብሩት ቀርተዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሰኞ ነሐሴ 13/2016 ዓ. ም. እንዳረጋገጠው፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጦር መሣሪያ ንግድ ስምምነት ሥራ ላይ ከዋለበት ከአሥር ዓመታት ወዲህ አንዳንድ የዓለም ታላላቅ የጦር መሣሪያ ላኪ አገራት ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን በመጠቀም ሕጎቹን በግልፅ ችላ በማለት እና ይህም ጋዛን ጨምሮ በግጭት ቀጠናዎች ውስጥ በሕይወት ላይ ከፍተኛ ጥፋት ማስከተሉን ገልጿል።

ካሪታስ አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግን እንዲያከብሩ አሳስቧል
የካቶሊክ የበጎ አድራጎት ድርጅት ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ ልዩ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራትን “በመርህ ላይ የተመሠረቱ የሰብዓዊነት ተዋናይ እሴቶቻቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ እና በዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ ጥሰት ተባባሪ ከመሆን እንዲቆጠቡ እና ከወታደራዊ ድጋፍ ይልቅ ሕጉን የሚጥሱ ተዋናዮችን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በመግለጫው አሳስቧል።

መግለጫው በማከልም፥ “ይህ መዘናጋት የሰብዓዊ ዲፕሎማሲ በአንድ በኩል ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ ጥሰቶችን በሚያወግዙ አገራት፣ በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ ጥሰቶችን የሚፈጽሙ መንግሥታት በሚሰጡት ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ መበላሸቱን ይቀጥላል” ሲል ገልጿል።

ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ በማከልም፥ ለአደጋ የተጋለጡት ብሔራዊ የሰብዓዊነት ዕርዳታ ሠራተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን አስታውሶ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2024 የወጣው የሰብዓዊነት እና የዓለም አቀፍ አንድነት ኤጀንሲዎች ደህንነት ፎረም ሪፖርት እንደሚያሳየው፥ ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ በአገር አቀፍ እና አገር በቀል ድርጅቶች ውስጥ የተጎዱት ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን እና ከዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ሲወዳደር ብልጫ እንዳለው አስረድቷል።

ሰብዓዊነትን የሚያስጠብቁ ውጤታማ እርምጃዎች ሊኖሩ ይገባል
ይሁን እንጂ ብዙዎቹ በቀጥታ የተቀጠሩት ወይም እንደ ዓለም አቀፍ ለጋሾች እና ድርጅቶች የቅርብ አጋር ሆነው የሚሠሩት የብሔራዊ ግብረሰናይ ሠራተኞች ሞት፣ ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች ያነሰ የሚዲያ ሽፋን እንደሚያገኝ ታውቋል።

ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ ለአውሮፓ ኅብረት በላከው መልዕክቱ፥ “የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች ደህንነት ለማረጋገጥ ውጤታማ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እና ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፎችን እንዲደረጉ፣ በዕርዳታ ሥራ ላይ እያሉ ለተገደሉት ተጠያቂነት እንዲኖር እና ለክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች ከፍተኛ የፖለቲካ እና የሚዲያ ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠይቆ፥ በዚህ መንገድ በማኅበረሰባቸው ውስጥ የሚገኙትን እና ሕዝባቸውን ለመርዳት የወሰኑትን የዕርዳታ ሠራተኞች መጠበቅ እና መርዳት እንችላለን” ሲል መልዕክቱን አጠቃሏል።

በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች መገደል
በዚህ ዓመት የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች የመጨረሻውን ዋጋ ከከፈሉባቸውና ከሲቪሎች ጋር በመሆን በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ምሥራቃዊ ግዛቶች ውስጥ ስድስት የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች የተገደሉበት እና በጥር እና በሰኔ ወር መካከል አሥራ አንድ ሠራተኞች የታፈኑባቸው ሌሎች ወሳኝ አካባቢዎች ሲገኙ፥ በመስክ ላይ ባሉ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞችን በቀጥታ ያነጣጠሩ ከ200 በላይ ክስተቶች መመዝገባቸው ታውቋል።

በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪ አቶ ብሩኖ ሌማርኪስ ሰኞ ነሐሴ 13/2016 ዓ. ም. ባስተላለፉት መልዕክት፥ “የእነዚህ ግድያዎች እና ስቃዮች አሳሳቢነት ቢኖራቸውም ዓለም አቀፉ ማኅበርሰብ በአሰቃቂ ሁኔታዎች ላይ ቁጣውን አልገለጸም” ሲሉ በምሬት ተናግረዋል።

በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በእነዚህ ቀውሶች ለተጎዱ ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ቁርጠኝነት ቢኖራቸውም ለ2024 ዓ. ም. ለቀረበው የሰብዓዊ ዕርዳታ የገንዘብ ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ 35 በመቶ ብቻ እንደሆነ እና ይህም ዕርዳታ ያልደረሳቸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ለአደጋ የተጋለጡ ሰዎች መኖራቸውን በመግለጽ ተጨማሪ የልገሳ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ለተግባራዊነቱ መነሳት
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ቀንን “WHD” ያወጀው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2003 ዓ. ም. በባግዳድ በሚገኝ ካናል ሆቴል ላይ በተፈፀመው የቦምብ ጥቃት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢራቅ ልዩ ተወካይ ሴርጂ ቪዬራ ዴ ሜሎን ጨምሮ 22 የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች ከተገደሉበት ከአምስት ዓመታት በኋላ እንደ ነበር ይታወሳል።

ለዘንድሮ በዓል የተመረጠው ጭብጥ “ለሰብዓዊነት እንነሳ” የሚል ጥሪ የሚያቀርብ ሲሆን፥ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪ አቶ ብሩኖ ሌማርኪስ ሰኞ ነሐሴ 13/2016 ዓ. ም. ባስተላለፉት መልዕክት፥ ሲቪሎችን እና የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞችን ከጥቃት ለመጠበቅ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ፥ በዕርዳታ ሠራተኞች እና በሲቪሎች ላይ ጥቃቶችን የሚፈፀሙ ወንጀለኞችን የመክሰስ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ አሳስበው፥ “ሲቪሎችን እና የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞችን ከአደጋ መጠበቅ የሚያቅተን ከሆነ እና የሰብዓዊ መብቶች መሠረታዊ ሕጎች ማስከበር ከተሳነን በችግር ላይ የወደቁ ሰዎች ማስታገስ አንችልም” ስሉ አስረድተዋል።

 

20 August 2024, 16:07