ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፤ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፤  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ "በሕይወት ውስጥ አስፈላጊው በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ነው" ማለታቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሰሜን ጣሊያን ሪሚኒ ከተማ የ 2024 ዓ. ም. ስብሰባ ተሳታፊዎች በላኩት መልዕክት፥ የስብሰባው ተካፋዮች ልባቸውን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ በመመለስ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች እንዲለምኑ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተለምዶ የሪሚኒ ስብሰባ ተብሎ ለሚጠራው እና በሕዝቦች መካከል ለሚደረገው የ 2024 ዓ. ም. የወዳጅነት ስብሰባ ተሳታፊዎች መልዕክት ልከዋል።

ታዋቂ ፖለቲከኞች፣ ሥራ ፈጣሪዎች፣ የሃይማኖት እና የባሕል ተወካዮች፣ ምሁራን፣ አርቲስቶች፣ አትሌቶች እና ሌሎችም የእውነታውን ውበት ለማግኘት ባላቸው ፍላጎት ተነሳስተው በባሕላዊ ልምድ በሰሜን ጣሊያን ሪሚሊ ከተማ በየዓመቱ ይሰባሰባሉ።

ሰኞ ነሐሴ 13/2016 ዓ. ም. በቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ በሆኑት በብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ተፈርሞ ይፋ የሆነው የቅዱስነታቸው መልዕክት፥ “የሚያስፈልገንን ነገር ካልሆነ ሌላ ምን እንፈልጋለን?” የሚለውን የዘንድሮው ስብሰባ መሪ ሃሳብ እንደሚያጎላ ተመልክቷል።

የሕይወትን እውነተኛ ትርጉም መፈለግ
የቅዱስነታቸው መልዕክት በዘመኑ ፈተናዎች መካከል “የሕይወት ምስጢር እና የእውነታው ዋና አካል የሆነውን የፍለጋ ወሳኝ ጠቀሜታን የሚገልጽ እና የሕይወትን ውበት ለመፈለግ ለሚደረገው ጥረት የሚያበረታታ እንደሆነም ተመልክቷል።

ርዕሥ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የስብሰባው ተሳታፊዎች በዘመናዊው ሕይወት ትግል ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት ልብን በመክፈት እያንዳንዱ ሰው ስለራሱ፣ ስለ ጎረቤቱ እና ስለ እውነታ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ የማሰላሰል ጥሪን እንዲያዩ አሳስበዋል።

ይህ ደግሞ በሕይወታችን ውስጥ እጅግ አስፈላጊው ነገር ቁሳዊ ነገሮች ወይም ስኬቶች ሳይሆኑ ነገር ግን እኛን የሚደግፈን ጉዟችንን እምነታችንን እና ተስፋችንን መሠረት በማድረግ ማለትም ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ወዳጅነት በውስጣችን የሚንፀባረቀውን፣ ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነቶች የሚያሳይ እንደሆነ ተገልጿል።

እጅግ አስፈላጊው በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ነው!
የዘንድሮው መልዕክት በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለእምነት አስተምህሮ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ያደረጉትን ንግግር “እጅግ አስፈላጊ የሆነው፣ እጅግ የሚያምር፣ እጅግ ማራኪ እና እንዲሁም ለእኛ አስፈላጊ የሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ነው” ያሉትን የሚያስታውስ እንደሆነ ተመልክቷል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሪሚኒ ከተማ ስብሰባቸውን በማካሄድ ላይ ለሚገኙት ያላቸውን አድናቆት እና ድጋፍ ገልጸው፥ ሁሉም ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ሊገኝበት እና በእጅም ሊዳሰስ ለሚችልባቸው ቦታዎች ሕይወትን በመስጠት በቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ውስጥ በንቃት በመተባበር ለውጥ የማምጣት ሃላፊነት ያለባቸው እንዲሆኑ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2024 ዓ. ም. በሪሚኒ የሚካሄደው ስብሰባ፥ ብዙዎች አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ፈላጊዎች እንዲሆኑ እና ለወንጌል ምስክርነት ያላቸውን ፍቅር፥ ከሁሉም ባርነት ነፃ የመውጣት ምንጭ፣ የሰውን ልጅ የሚፈውስ እና የሚቀይር ኃይል በልባቸው ውስጥ እንደሚያሳድግ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

 

20 August 2024, 16:49