ካቶሊክ ምዕመናን በጋራ አምልኮ ሥነ-ሥርዓት ላይ ካቶሊክ ምዕመናን በጋራ አምልኮ ሥነ-ሥርዓት ላይ  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በጋራ የሚቀርብ የአምልኮ ጸሎት ለቤተ ክርስቲያን ሕይወት አስፈላጊ እንደሆነ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሰሜን ጣሊያን ሞዴና-ኖናንቶላ ከተማ በመካሄድ ላይ ለሚገኝ 74ኛው ብሔራዊ የጋራ አምልኮ ሳምንት ተሳታፊዎች መልዕክት ልከዋል። “ስሙን የሚመሰክሩ ከንፈሮች ፍሬ” በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው ይህ ስብሰባ በጋራ በሚቀርቡ የአምልኮ ጸሎቶች፣ በመንፈሳዊ ዜማዎች፣ በጸጥታ በሚደረጉ ጸሎቶች እና በአምልኮ አገልግሎቶች አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጣሊያን ሞዴና-ኖናንቶላ ከተማ ከነሐሴ 20-23/2016 ዓ. ም. ድረስ በመካሄድ ላይ ለሚገኝ 74ኛው አገር አቀፍ የአምልኮ ሥርዓት ሳምንት ባስተላለፉት መልዕክት፥ በኅብረት የሚቀርብ የአምልኮ ጸሎት በግል ከሚቀርብ ጸሎት በተለየ መንገድ እንዴት የጋራ ልምድ እንደሚሆን አስታውሰዋል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስን የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፥ የአምልኮ ጸሎት በኢየሱስ ክርስቶስ ጸሎት በመሳተፍ በመንፈስ ቅዱስ በኩል ወደ እግዚአብሔር አብ የሚቀርብ ጸሎት መሆኑን የስብሰባው ተሳታፊዎችን አሳስበዋል።

በፍላጎቶች ላይ ከሚያተኩሩ የግል ጸሎቶች በተለየ፥ በኅብርተ የሚቀርብ የአምልኮ ጸሎት ምእመናንን አንድ አካል እንደሚያደርጋቸው፣ ይህም በቤተ ክርስቲያን የጋራ ጸሎት እንዲካፈሉ እንደሚያስችላቸው እና ይህ የአንድነት ልምድ ምዕመናንን በየጊዜው እና በየቦታው የሚያገናኝ በመሆኑ የክርስትና ሕይወት የማዕዘን ድንጋይ ነው ሲሉም አክለዋል።

የጋራ አምልኮ ጸሎትን የመካፈል ጥበብ
የአምልኮ ጸሎትን የመካፈል ጥበብ በሚለው የሳምንቱ ውይይቶች ማዕከላዊ ጽንሰ-ሃሳብ ላይ በማትኮር መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ይህ መደበኛ የሆኑ የአምልኮ ሥርዓቶችን ማክበርን ብቻ ሳይሆን የአክብሮት እና የተሳትፎ አመለካከትን የሚያካትት፣ ማኅበረሰቡን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወደ ጥልቅ ኅብረት የሚስብ መሆኑን ተናግረዋል።

በአምልኮ ሥርዓት አከባበር አማካኝነት የሚሰጠው ጸጋ የተሳታፊዎችን ሕይወት በመንካት ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ ጠቁመው፥ ይህም በቤተ ክርስቲያን ምስጢረ ጥምቀትን የተቀበሉ ምዕመናን ወደ ግለኝነት ከማዘንበል ይልቅ በጸሎት ላይ በምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የጋራ ማንነት እንዲኖራቸው የሚጋብዝ መሆኑን አስረድተዋል።

የመንፈሳዊ መዝሙር ሚና
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አጽንዖት ከሰጧቸው ቁልፍ ገጽታዎች መካከል አንዱ መንፈሳዊ መዝሙር በአምልኮ ሥርዓት ውስጥ ያለው ሚና ሲሆን፥ መንፈሳዊ ሙዝሙር ለአምልኮ ሥርዓት አከባበር ወሳኝ እንደሆነ እና የእምነትን ምስጢር በማስተላለፍ ረገድ ልዩ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ምእመናን በኅብረት ሲዘምሩ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ተቆራኝተው እምነታቸውን እንደሚጠብቁ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ የተናገሩትን ጠቅሰው፣ የጋራ ዝማሬ መንፈሳዊ ይዘቱን እንደሚያጎላው ገልጸው፥ የድምጻቸው ውህደትም ምእመናን በአንድነት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ የሚያደርጉትን የጋራ ጉዞን ያሳያል ብለዋል።

በአምልኮ ውስጥ የጽሞና አስፈላጊነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳት ፍራንችስኮስ ለስብሰባው ተሳታፊዎች የላኩት መልዕክት፥ ብዙውን ጊዜ በጫጫታ እና በማይቆም እንቅስቃሴ ለሚታወቅ ዓለም፥ በአምልኮ ሥርዓት ወቅት ያለው የጽሞና ጊዜ ዋጋ እንዳለው ትኩረት በመስጠት ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው በአምልኮ ሥርዓት ወቅት የሚኖር የጽሞና ጊዜ የጸሎት መንፈስን የሚቀንስ ሳይሆን ምእመናን እግዚአብሔርን ማዳመጥ የሚችሉበት፣ የሚያስተነትን ልብን የሚያዳብሩበት እና በመንፈስ ቅዱስ ለመለወጥ የሚፈቅዱበት ትርጉም ያለው ጊዜ እንደሆነ ገልጸው፥ ይህ የተቀደሰ የጽሞና ጊዜ ምዕመናን ከመለኮታዊው ኃይል ጋር እና እርስ በርስ እንዲተሳሰሩ የሚያስችላቸው ቁልፍ የአምልኮ አካል እንደሆነ አስረድተዋል።

የአምልኮ ሥርዓት አገልግሎት እና የሲኖዶሳዊነት መንፈስ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድሮ በጣሊያን ለተዘጋጀው ብሔራዊ የሥርዓተ አምልኮ ሳምንት አስፈላጊ ገጽታን በማብራት በአምልኮ ሥርዓት አገልግሎቶች ላይም ትኩረትን ሰጥተው፥ አገልግሎቶቹ የተግባር ሚናዎች ብቻ ሳይሆኑ መንፈስ ቅዱስ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጣቸው ልዩ ልዩ ስጦታዎች መግለጫዎች መሆናቸውን አስምረውበታል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእነዚህ ልዩነቶች ውስጥ የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንደሚገለጽ፥ በንቁ ተሳትፎ እና በቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ውስጥ የጋራ ሃላፊነትን እንደሚያበረታታ እና እነዚህ አገልግሎቶች በትህትና እና በአገልግሎት መንፈስ እንዲተገበሩ አሳስበው፣ ወደ ግለኝነት ስሜት የሚመሩ ዝንባሌዎችን በማስወገድ ቀጣይነት ያለው ልምምድ እንዲደረግ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

 

27 August 2024, 15:21