ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ወደ ሮም ባደረጉት በረራ ላይ መግለጫ ሲሰጡ  ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ወደ ሮም ባደረጉት በረራ ላይ መግለጫ ሲሰጡ   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የጋዛን ጦርነት ለማስቆም የተወሰደ እርምጃ የለም ማለታቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእስያ እና ኦሼኒያ አኅጉራት ያደረጉትን 45ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ወደ ሮም ሲመልሱ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የመጨረሻ ምዕራፍ ከሆነች ሲንጋፖር ተነስተው ወደ ሮም ባደረጉት በረራ ላይ በጋዛ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ጨምሮ የተለያዩ ርዕሠ ጉዳዮችን በማስመልከት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፥ በጋዛ ውስጥ የተጎጂዎች ቁጥር ከ41,000 በላይ መድረሱን እና ጦርነቱን ለማስቆም የተወሰደ እርምጃ አለመኖሩን በሐዘን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአሜሪካ ሊካሄድ በታቀደው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ዜጎች ትክክለኛ ህሊናን ተጠቅመው በምርጫው ሊሳተፉ እንደሚገባ አሳስበው፥ አገሪቱ ያላትን የውርጃ እና የጸረ ስደተኛ አቋም አውግዘዋል። ከቻይና ጋር ሲደረግ የቆየውን ስምምነት እና ያለውን አዎንታዊ ምላሽ ገልጸው አገሪቱ ለቤተ ክርስቲያን መልካም ተስፋ እንደሆነች ተናግረዋል።

“ሲንጋፖርን በዚህ ሁኔታ ​​አገኛታለሁ ብዬ አልጠበኩም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “የምሥራቁ ዓለም ኒውዮርክ” ብለዋት እንደሚጠሯት፣ ያደገች፣ ጨዋ ሕዝቦች ያሏት እና የታላቅ ሃይማኖታዊ ባሕል አገር እንደ ሆነች እና ከልዩ ልዩ የሃይማኖት ተቋማት ጋር ያደረጉት ውይይትም የወንድማማችነት ምሳሌ እንደነበር ገልጸዋል።

ስደተኞችን በተመለከተ ሲናገሩ በአገሪቱ ውስጥ መድልዎ እንዳለ አልተሰማኝም ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ሰማይ ጠቀስ የቅንጦት ፎቆች እና ሌሎችም በንጽሕና እና በጥሩ ሁኔታ የተያዙ መሆናቸውን ገልጸው፥ ባሕላቸው እና በተለይ በመጨረሻው ቀን ከተማሪዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ ደስ እንደተሰኙ አስረድተዋል። የሲንጋፖርን ዓለም አቀፍ ሚና በተመለከተ፥ ሲንጋፖር የተለያዩ ባሕሎችን የሚስብ ዓለም አቀፍ ካፒታል ያላት አገር እንደሆነች ገልጸዋል።

“ወደማያውቁት አገር ሲኬድ የሚማሩት ብዙ አዲስ ነገር ሁል ጊዜ ይኖራል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ እያንዳንዱ ሰው እና አገር የተለያዩ ጸጋዎች እንዳላቸው ገልጸው፥ በእርስ በርስ ግንኝነት መካከል ወንድማማችነት አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው ብለዋል። በቲሞር-ሌስቴ ውስጥ ብዙ ልጆች ሲኖሩ ነገር ግን በሲንጋፖር ውስጥ ግን ብዙ ልጆችን አለማየትቸውን ተናግረው፥ ምናልባት ይህ ትምህርት ሊሆን እንደሚችል እና ልጆች የመጪው ጊዜ ተስፋዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።

የቲሞር-ሌስቴ ሕዝብ ትሑት እና አስደሳች የቤተሰብ ባሕል እንዳለው የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ ነገር ግን እንደ አዞ ጎጂ የሆኑ እና ከውጭ የሚመጡ ሃሳቦች ባሕላቸውን እና በመካከላቸው ያለውን ስምምነት ሊያበላሹ እንደሚችሉ በማስረዳት ለቲሞር-ሌስቴ ሕዝብ ጥልቅ ፍቅር እንዳላቸው ተናግረዋል።

ሁሉም ሃይማኖቶች ሊከበሩ እንደሚገባ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ነገር ግን በሃይማኖት እና በቡድን መካከል ልዩነት መኖሩን ገልጸው፥ ሃይማኖት ምንም ይሁን ምን ዓለም አቀፋዊነት ሲኖረው ነገር ግን በሃይማኖት ስም የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ሁሌም የተለየ አጀንዳ እንዳለው አስረድተዋል።

“በማደግ ላይ ባሉ አገራት ውስጥ ለዲሞክራሲ መታገል የተለመደ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ እንደሚለው በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ያለውን ግንኙነት ማረጋገጥ አስፈላጊ እንደሆነ መናገሩን አስታውሰው፥ ኢንዶኔዥያ በማደግ ላይ ያለች ሀገር ብትባልም ሊኖራት የሚፈልገው አንዱ ልማት ማኅበራዊ ግንኙነት ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ከቻይና ጋር እየተካሄደ ባለው ውይይት ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥እስካሁን የተገኙት ውጤቶች ጥሩ እንደሆኑ ተናግረው፥ የብጹዓን ጳጳሳት ሹመትን በተመለከተ ነገሮች በመልካም ፈቃድ እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ከቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ጋር እንደተነጋገሩ እና ሁኔታዎች በጥሩ መንገድ እየሄዱ መሆናቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። ቻይና ጥንታዊ ባህል ያላት ጥሩ አገር በመሆኗ እንደሚያደንቋት እና እንደሚያከብሯት ገልጸው ወደ ፊት ሊጎበኟት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

በተለያዩ የአስተዳደር ሥርዓቶቿ የመነጋገር እና የውይይት አቅም ያላት ቻይና ለቤተ ክርስቲያን ቃል ኪዳን እና ተስፋ ነች ብዬ አምናለሁ ብለዋል። በእርግጠኝነት ግጭቶችን በማስወገድ ከቻይና ጋር መተባበር ይቻላል ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በዚህ ዙሪያ ከቻይና መንግሥት ጋር እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ስደተኞችን ማባረር እና ሕፃናትን መግደል ሁለቱም ሕይወትን መቃወም እንደሆነ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዚህ ጉዳይ እርሳቸው መወሰን እንደማይችሉ፥ ነገር ግን ለስደተኞች የሥራ ዕድልን እና መስተንግዶን መከልከል ከባድ ኃጢአት መሆኑን ለመግለጽ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

ውርጃን በተመለከተ ሳይንስ እንደሚናገረው ከተፀነሰ በኋላ በአንድ ወር ውስጥ ሁሉም የሰውነት አካላት እንደሚታዩ ገልጸው፥ ፅንስን ማስወረድ ነፍስን መግደል በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን በጥብቅ ታወግዘዋለች ብለዋል። ይንህ ጉዳይ ግልጽ ማድረግ አለብን ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ስደተኞችን ወደመጡበት መላክ፣ እንዲያድጉ አለመፍቀድ እና የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው አለመፍቀድ ስህተት እና ጭካኔ ነው ብለው፥ ልጅን ከእናት ማሕፀን ውስጥ ማስወጣት በሕይወት ላይ የሚፈጸም ግድያ እንደሆነ አስረድተዋል።

በፖለቲካ ሥነ-ምግባር ረገድ ድምጽ አለመስጠት ጥሩ አይደለም ያሉት ቅዱስነታቸው፥ አንድ ሰው መምረጥ እንደሚገባ እና ቀላል የሚባሉ ክፋቶች መምረጥ እንደሚገባ ተናግረው፥ ቀላል እና ከባድ የሚባሉ ክፋቶች የትኞቹ እንደሆኑ እያንዳንዱ ሰው እንደ ህሊናው ማሰብ እና መወሰን አለበት ብለዋል።

የጋዛ ግጭት ወደ ዌስት ባንክ ሊሸጋግር ይችላል የሚለውን ስጋት ለመቅረፍ ቅድስት መንበር እየሠራች እንደምትገኝ ቅዱስነታቸው ተናግረው፥ የጋዛን ሁኔታ በየቀኑ እንደሚከታተሉት እና እዚያ የምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በትምህርት ቤቷ ውስጥ ለሚገኙ 600 ክርስቲያን እና ሙስሊም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ዕለታዊ ዕርዳታ በማድረግ ላይ እንደምትገኝ አስረድተዋል።

በዚህ ጦርነት ሕጻናት ሲገደሉ ማየት እና ትምህርት ቤቶች በቦንብ ሲደበደቡ ስንሰማ በጣም የሚያስደነግጥ እና አሰቃቂ ነው ብለዋል። አንዳንድ ጊዜ “ራስን ለመከላከል የሚደረግ ጦርነት ነው ይባል እንጂ ሁኔታው ከዚህ በላይ እንደ ሆነ ይሰማኛል” ብለው፥ ይህን በማለታቸው ይቅርታን ጠይቀው ነገር ግን ወደ ሰላም የሚወስዱ እርምጃዎች አለመወሰዳቸውን ተናግረዋል።

በሲንጋፖር ውስጥ የሞት ቅጣት መኖሩን ያልተናገሩት ወደ አእምሮው ባለመምጣቱ ምክንያት እንደሆነ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ የሞት ቅጣት የማይሠራ እና ቀስ በቀስ ሊወገድ የሚገባ ተግባር እንደሆነ፥ ብዙ አገራት የሞት ቅጣትን የሚከለክል ሕግ ቢኖራቸውም በተግባር እንደማይፈጽሙት ገልጸው፥  የሞት ቅጣት መቆም ያለበት እና የተሳሳተ ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል።

በቬንዙዌላ ያለውን ሁኔታ በቅርብ እንዳልተከታተሉት የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ ነገር ግን ለአገሪቱ መሪዎች የሚሰጡት መልዕክት ወደ ውይይት በመመለስ ሰላምን መፈለግ እንደሆነ ተናግረው፥ አምባገነን መንግሥታት ምንም ፋይዳ እንደሌላቸው እና ፈጠነም ዘገየም ሁልጊዜም መጨረሻቸው ክፉ እንደሚሆን አስረድተዋል።

በቬንዙዌላ ሰላምን ለማምጣት መንግሥት እና ሕዝብ የተቻላቸውን ሁሉ ማድረግ አለባቸው ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ዝርዝር ሁኔታዎችን ስለማያውቁ የፖለቲካ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል። የአገሪቱ ብጹ ዓን ጳጳሳት ድምጻቸውን እንዳሰሙ አውቃለሁ ያሉት ቅዱስነታቸው፥ መልዕክታቸውም መልካም እንደሆነ ተናግረዋል።

ወደ አርጄንቲና የመሄድ ዕቅድ እንዳላቸው የተጠየቁት ቅዱስነታቸው፥ አገራቸው በመሆኗ ሊጎበኟት ቢፈልጉም ነገር ግን እስካሁን ምንም አለመወሰናቸውን ተናግረው፥ በቅድሚያ መፍታት ያለባቸው ሌሎች ብዙ ነገሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝት ላይ የተሳተፉትን እና ከጎናቸው የሆኑትን ሰዎች እና ድርጅቶች በሙሉ አመስግነዋል።

 

14 September 2024, 16:43