የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለሰላም በመጸለይ የታራሚዎች መብት እንዲከበር ጥሪ አቅርበዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጦርነት ውስጥ በሚገኙት አገራት ሰላም እንዲወር እና የሰዎች ስቃይ እንዲያበቃ፣ እንዲሁም የታራሚዎች መብት እንዲከበር በቀጣይነት ጸሎት እንዲደረግ ተማጽነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ መስከረም 12/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የእኩለ ቀኑን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ካደረሱ በኋላ ባደረጉት ንግግር፥ በጎ ፈቃድ ላላችው ሰዎች በሙሉ ሰላምታ አቅርበው ሳያቋርጡ ለሰላም እንጸልዩ አደራ ብለዋል።

“ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ለሰላም መጸለይን እንቀጥል” በማለት ያሳሰቡት ቅዱስነታቸው በጦርነት ግንባሮች ከፍተኛ ውጥረት መኖሩንም ተናግረዋል።

በዩክሬን፣ በፍልስጤም፣ በእስራኤል፣ በምያንማር እና ጦርነት ባሉባቸው በርካታ አካባቢዎች ውስጥ የሚደረሰውን መከራ በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች መዘንጋት እንደሌለባቸው በማሳሰብ፥ “ሰላምን የሚጠይቁ ሕዝቦች ድምፅ ይሰማ” ሲሉ ተማጽነዋል።

የታራሚዎች ስብዕና ይከበር!
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ታራሚዎች የሚገኙበትን ሁኔታ ለማስገንዘብ በተካሄደው ሰልፍ ላይ ለተገኙት እና ለመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

በመጨረሻም “ሁሉም ሰው ሊሳሳት ይችላል፤ ከስህተት መታረም ደግሞ ወደ መልካም እና ታማኝ ሕይወት ለመመለስ ነው” ብለው፥ ታራሚዎች በክብር እንዲያዙ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

 

23 September 2024, 17:28