ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የሲንጋፖር ወጣቶች በሃይማኖቶች ውይይት ወደ አንድነት እንዲደርሱ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሲንጋፖር ካቶሊክ መለስተኛ ኮሌጅ ውስጥ ከልዩ ልዩ ሃይማኖቶች የመጡ ወጣቶችን ያሳተፈ የሃይማኖቶች የጋራ ውይይት ተካፍለው መልዕክት አስተላልፈዋል። ከልዩ ልዩ የሃይማቶት ተቋማት ለመጡት ወጣቶች ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ለአንድነት በጋራ እንዲሠሩ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች እንዲሆኑ እና የተማሩትን ለትውልድ የሚያካፍሉ እንዲሆኑ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሲንጋፖር ወጣቶች ጋር ዓርብ መስከረም 3/2017 ዓ. ም. ተገናኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ በሲንጋፖር ልዩ ልዩ እምነቶችን የሚከተሉ ወጣቶች በመካከላቸው አንድነትን እና ተስፋን ለማሳደግ በርትተው እንዲሠሩ አሳስበዋል።

በስብሰባው ላይ ከ50 በላይ ትምህርት ቤቶች እና ሃይማኖታዊ ድርጅቶች የተውጣጡ 600 የሚሆኑ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፥ ይህም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእስያ እና ኦሼኒያ በሚገኙ አራት አገራት ማለትም በኢንዶኔዥያ፣ በፓፑዋ ኒው ጊኒ፣ በቲሞር-ሌስቴ እና በሲንጋፖር ያደረጉትን 45ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ወደ ሮም ከመመለሳቸው በፊት የተሳተፉበት የመጨረሻ ዝግጅት እንደሆነ ታውቋል።

የሲንጋፖር ወጣቶች የገቡት ቃል ኪዳን
በዝግጅቱ ላይ ወጣቶቹ የወደፊቱ ትውልድ ለአንድነት እና ለተስፋ እንደሚሠራ ገልጸው፥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግር በኋላ በገቡት ቃል ኪዳን፥ “እኛ መጪው ትውልድ በልዩ ልዩ እምነት ተከታዮች መካከል ያለውን አብሮ የመኖር ባሕልን የሚያጎለብት ትብብር እና ወዳጅነት በማሳደግ ለአንድነት እና ለተስፋ ብርሃን እንሠራለን” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሂንዱ፣ ከሲክ እና ከካቶሊክ እምነት ከመጡት ምስክርነት ሰጪ ወጣቶች የቀረበላቸውን ሰላምታ ከተቀበሉ በኋላ በግል የእምነት ጉዞአቸው ብርታትን በመመኘት ወደ ጋራ ጥቅም አብረው እንዲጓዙ ተማጽነዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ  በሃይማኖቶች የጋራ ውይይት ላይ ተገኝተው
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሃይማኖቶች የጋራ ውይይት ላይ ተገኝተው

“አምባገነንነት ውይይትን አይፈቅድም”
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከወጣቶቹ ጋር ባደረጉት ውይይት ያለ ችግር እና ፈተና የመኖር ምኞትን ትተው ወደ ፊት እንዲራመዱ እና ገንቢ ትችቶችን ለማቅረብ ድፍረት እንዲኖራቸው ጋብዘዋል። “እንደ ወጣትነትህ የምትወያይ ከሆነ እንደ ዜጋና እንደ ማኅበረሰብ አባል ነግሮችን ልታከናውን ትችላለህ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በታሪክ ዘመናት ሁሉ “የአምባገነንነት የመጀመሪያው ሥራ ውይይትን ማስወገድ ነው” ብለዋል።

“ፍርሃትን አስወግዱ!”
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለወጣቶቹ በተናገሩት ማሳሰቢያ ለሚያጋጡ አደጋዎች ሃላፊነትን እንዲወስዱ እና በማኅበራዊ ሕይወት ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አሳስበው፥ “ፍርሃት ሽባ ሊያደርግህ የሚችል የአምባገነንነት አመለካከት ነው ሲሉ” ገልጸው፥ ወጣቶች እንደማንኛውም ሰው ስህተት መሥራታቸው የማይቀር መሆኑን ተናግረዋል። “ስሕተት መሥራት የተለመደ ነገር ቢሆንም ነገር ግን የበለጠ አስፈላጊው ስሕተትን ካመኑ በኋላ ሕይወትን እንደገና መጀመር ነው” ብለዋል።

በምስክርነቶች መካከል የተነሱትን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ “እነዚህ መሣሪያዎች ጠቃሚ ቢሆኑም ነገር ግን የእነርሱ ተገዥዎች እንዳንሆን መጠንቀቅ አለብን” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሃይማኖቶች የጋራ ውይይት ላይ በተገኙበት ወቅት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሃይማኖቶች የጋራ ውይይት ላይ በተገኙበት ወቅት

“ሁላችንም የእግዚአብሔር ልጆች ነን!”
ቅዱስነታቸው መልዕክታቸውን በመቀጠል፥ በስብሰባው የተገኙት በሙሉ በጸሎት እንዲተባበሯቸው ጋብዘዋል። “እግዚአብሔር ሁላችንንም ይባርከን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ጊዜ እያለፈ በሄደ ቁጥር ወጣቶች ሳይሆኑ ትልልቆች እና አያቶች እንደሚሆኑ በማሳሰብ ይህን መልዕክት ለሌሎችም እንዲያስተላልፉ አደራ ብለዋል።

“እግዚአብሔር የሁሉ አምላክ ነው!”
“እግዚአብሔር የሁሉ አምላክ ነው፤ የሁሉ አምላክ ከሆነ እኛ ሁላችንም የእግዚአብሔር ልጆች ልጆች ነን” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ለመድረስ የምንጓዝባቸው መንገዶች ናቸው” በማለት ከተለያዩ ቋንቋዎች ጋርም ካነጻጸሩ በኋላ “እግዚአብሔር የሁሉም አምላክ ነው” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በሲንጋፖር የልዩ ልዩ እምነቶች ተከታይ ወጣቶች በሃይማኖቶች መካከል የጋራ ውይይቶችን በማካሄድ እና እርስ በርስ በመከባበር ላሳዩት ምሳሌነት ካመሰገኗቸው በኋላ በጸሎትም እንደሚያስታውሷቸው አረጋግጠውላቸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በሲንጋፖር ከወጣቶች ጋር ያደረጉት የሃይማኖቶች ውይይት
13 September 2024, 16:50