ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቤልጂየም ወሲባዊ ጥቃት የተፈጸመባቸውን አግኝተው አነጋገሩ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቤልጂየም ወሲባዊ ጥቃት የተፈጸመባቸውን አግኝተው አነጋገሩ  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቤልጂየም ቤተ ክኅነት ወሲባዊ ጥቃት የተፈጸባቸውን አግኝተው አጽናኑ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጉብኝታቸው ሁለተኛ አገር በሆነች ቤልጂየም ውስጥ እንደሚገኙ ሲታወቅ፥ የዓርብ ዕለት ጉብኝታቸውን ከማጠቃለላቸው በፊት በቤተ ክኅነት ወሲባዊ ጥቃት የተፈጸመባቸውን ሰዎች አግኝተው አነጋግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቤልጂየም ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጉብኝታቸው የመጀመሪያ ቀን ዓርብ መስከረም 17/2017 ዓ. ም. ከካኅናት በኩል ወሲባዊ ጥቃት ከተፈጸመባቸው 17 ሰዎች ጋር ተሰብስበው ተነጋግረዋል።

የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ዓርብ መስከረም 17/2017 ዓ. ም. ማምሻውን በሰጠው የቴሌግራም መግለጫ፥ ስብሰባው የተካሄደው ብራስልስ ውስጥ በሚገኝ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት እንደነበር አስታውቋል።

“ከሁለት ሰዓታት በላይ የፈጀው ስብሰባው የጥቃቱ ሰለባዎች የግል ታሪካቸውን እና ስቃያቸውን ለቅዱስነታቸው እንዲያካፍሉ ዕድል የሰጠ፣ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያኒቱ እየደረሰ ያለውን የመብት ጥሰት ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት የገለጸችበት ነበር” ሲል መግለጫው አስታውቋል።

የቅድስት መንበር መግለጫው “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰለባዎችን ልምድ በጽሞና ካዳመጡ በኋላ በደረሰባቸው ስቃይ የተሰማቸው ሐዘን እና ያላቸውን ቅርበት ገልጸውላቸዋል” ብሏል።

ቅዱስነታቸው የወሲባዊ ጥቃት ሰለባዎችን ለድፍረታቸው ከልብ ማመስገናቸው እና በልጅነት ዕድሜያቸው ከካህናት በተፈጸመባቸው ጥቃት እና በደረሰባቸው በደል የተሰማቸውን ከባድ ሐፍረት መግለጻቸውን መግለጫ ክፍሉ አክሎ አስታውቋል።

ቅዱስነታቸው በስብሰባው ማጠቃለያ ተጨማሪ ጥናት እንዲደረግ የጥቃቱ ሰለባዎች ያቀረቡትን ጥያቄ ከልብ መቀበላቸውን መግለጫው አስታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለቤልጂየም ባለስልጣናት ባደረጉት ንግግር በተለይ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንቅፋት የሆነውን እና በሕጻናት ላይ የተፈጸሙ አሳዛኝ ወሲባዊ ጥቃቶችን በማስታወስ ቤተ ክርስቲያን ጉዳዩን ለመፍታት በቁርጠኝነት እየተከታተለች እንደምትገኝ እንዲሁም ጉዳት የደረሰባቸውን በማዳመጥ እና በማጽናናት ከመሰል ጥቃጥ የመከላከል መርሐ-ግብሯን በአገሪቱ እና በመላው ዓለም ተግባራዊ ለማድረግ መነሳሳቷን መግለጻቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከመስከረም 16 እስከ መስከረም 19/2017 ዓ. ም. ድረስ በሉክሰምበርግ እና በቤልጂየም 46ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።


 

28 September 2024, 16:53