ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “በእስያ እና ኦሼኒያ አኅጉራት ውስጥ ሕያው እና አስደሳች እምነት አለ” ሲሉ ተናገሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በእስያ እና ኦሼኒያ አኅጉራት ከነሐሴ 27/2016 እስከ መስከረም 3/2017 ዓ. ም. ድረስ ሐዋርያዊ ጉብኝት አድርገው ተመልሰዋል። በዚህ 45ኛው የውጭ አገር ጉዞአቸው ኢንዶኔዥያን፣ ፓፑዋ ኒው ጊኒን፣ ቲሞር-ሌስቴ እና ሲንጋፖርን ጎብኝተዋል። ቅዱስነታቸው ከሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መልስ ሳምንታዊውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ለመከታተል መስከረም 8/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ንግግር አድርገዋል። ቅዱስነታቸው ወደ እስያ እና ኦሺኒያ አኅጉራት ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስታወስ ባደረጉት ንግግር፥ በጎበኟቸው አገራት ውስጥ ሕያው እና አስደሳች እምነት መኖሩን ተናግረዋል።

ክቡራትና እና ክቡራን፥  የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ንግግር ትርጉም ከማቅረባችን አስቀድመን በዕለቱ የተንበበውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

“አሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ወዳዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ። ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ አላቸው፥ ‘ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል። ስለዚህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተምሯቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ’” (ማቴ. 28: 16. 18-20)።

ክቡራት እና ክቡራን፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ያሰሙትን ንግግር ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እንደምን አደራችሁ! ዛሬ በእስያ እና በኦሼንያ አኅጉራት ስላደረግኩት ሐዋርያዊ ጉብኝት እናገራለሁ።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1970 የፀሐይ መውጫ ወደ ሆኑት ፊሊፒንስ እና አውስትራሊያ ረጅም ሐዋርያዊ ጉብኝት ያደረጉት የመጀመሪያው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ነበሩ። በዚህ ጉብኝታቸው ወቅት በተለያዩ የእስያ ሀገራት በኩል በማለፍ በሳሞአን ደሴቶች አጭር ቆይታ አድርገዋል። የማይረሳ ጉዞ ነበር! በዚህኛውም ሐዋርያዊ ጉብኝቴ የእርሳቸውን ምሳሌ ለመከተል ሞክሬ ነበር። ነገር ግን እርሳቸውን በጥቂት ዓመታት በዕድሜ ስለምበልጣቸው በአራት አገሮች ማለትም ኢንዶኔዥያን፣ ፓፑዋ ኒው ጊኒን፣ ቲሞር-ሌስቴን እና ሲንጋፖርን ብቻ ለመጎብኘት ወሰንኩ። እንደ ወጣት ኢየሱሳውያን ማድረግ የምፈልገውን በአረጋዊ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዕድሜ እንዳደርግ የፈቀደልኝን እግዚአብሔር አመሰግናለሁ!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ቲሞር ሌስቴ ሲደርሱ የተደረገላቸው የክብር አቀባበል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ቲሞር ሌስቴ ሲደርሱ የተደረገላቸው የክብር አቀባበል

ከዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝት መልስ በእርግጥ በአእምሮዬ የመጣው የመጀመሪያው ሃሳብ፥ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሳስብ እኛ አሁንም በጣም አውሮፓዊ አመለካከት ያለን ሰዎች ነን። ወይም እነርሱ እንደሚሉት “ምዕራባዊ” ነን። በእውነቱ ቤተ ክርስቲያን በጣም ትልቅ እና የበለጠ ሕያው ነች! ከማኅበረሰቦች ጋር በመገናኘት፣ የካህናትን፣ የገዳማውያት እህቶችን፣ የምእመናንን እና በተለይም የትምህርተ ክርስቶስ መምህራንን ምስክርነት በማዳመጥ ይህን በሙሉ በሚያስደስት መንገድ ለመመልከት ችያለሁ። ሰዎች ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ የሚያደርጉትን ሳይሆን በተግባራቸው እና በምስክርነታቸው ሌሎችን በመሳብ የሚያድጉ ቤተ ክርስቲያናትን ተመልቻያለሁ። 

በኢንዶኔዥያ አሥር በመቶ የሚሆኑት ክርስቲያኖች ሲሆኑ ከእነርሱ መካከል ሦስት በመቶው ካቶሊኮች ናቸው። ነገር ግን ያጋጠመኝ እጅግ የተከበረ ባሕል ያላት፣ ብዝሃነትን የማስማማት ዝንባሌ ያደረባት እና በዓለም ላይ ትልቁ የሙስሊም ቁጥር በሚገኝባት አገር ውስጥ ወንጌልን የመኖር እና የማሰራጨት ብቃት ያላት፣ ንቁ እና ህያው ቤተ ክርስቲያን ነበረች። በዚያ አውድ ውስጥ ርኅራኄ ክርስቲያኖች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት ለመመስከር እና በተመሳሳይም ከታላላቅ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ወጎች ጋር የሚገናኙበት መንገድ እንደሆነ ማረጋገጫ አገኘሁ። “እምነት፣ ወንድማማችነት እና ርህራሄ” የሚለው በኢንዶኔዥያ ላደረግሁት ሐዋርያዊ የጉብኝቴ መሪ ቃል ነበር። በእነዚህ ቃላት መሠረት ወንጌል በየቀኑ ወደ ሰዎች ሕይወት ውስጥ በሚገባ በተጨባጭ መንገድ ይገባል። ወንጌልን መቀበል የሞተው እና ከሞት የተነሳው የኢየሱስ ክርስቶስን ጸጋ ይሰጣል። እነዚህ ቃላት የጃካርታ ካቴድራልን በእስያ ከሚገኙት ትልቁ መስጊድ ጋር እንደሚያገናኘው ድልድይ ናቸው። በዚያች አገር ወንድማማችነት የወደፊት ዕጣ ፈንታ መሆኑን አይቻለሁ። ይህም ለፀረ-ስልጣኔ፣ ለሰይጣናዊ የጥላቻ እና የጦርነት ሴራዎች መልስ ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢንዶኔዥያው የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢንዶኔዥያው የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው

በፓፑዋ ኒው ጊኒ የምትገኝ የሚስዮናዊት ቤተ ክርስቲያን ውበት እንደገና አግኝቻለሁ። በግዙፉ የፓስፊክ ውቅያኖስ መካከል በርካታ ደሴቶች ተዘርግተዋል። በእነዚያ ደሴቶች ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ብሔረሰቦች ከስምንት መቶ በላይ ቋንቋዎችን ይናገራሉ። የፍቅርን መልዕክት በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ለማስተላለፍ ለሚወድ መንፈስ ቅዱስ ተስማሚ አካባቢ ነው።

በዚህ አካባቢ በተለየ መንገድ ዋና ተዋናዮች የነበሩት እና አሁንም ያሉት ሚስዮናውያን እና የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ናቸው። ከዛሬዎቹ ሚስዮናውያን እና የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ጋር ትንሽ መቆየት በመቻሌ ተደስቻለሁ። በውስጣቸው የጎሳ ግጭት፣ ጥገኝነት፣ የኢኮኖሚ ወይም የርዕዮተ ዓለም ቅኝ አገዛዝ የሌለበት፣ የወንድማማችነት እና አስደናቂ የተፈጥሮ አካባቢ እንክብካቤ አዲስ ሕይወት የሚገልጹ የወጣቶች ዘፈኖችን እና ሙዚቃዎችን በማዳመጥ ተገርሜአለሁ። ፓፑዋ ኒው ጊኒ በወንጌል “እርሾ” የተነሳሳች እና የሁለንተናዊ ዕድገት ሞዴል መገኛ መሆን ትችላለች። ምክንያቱም ያለ አዲስ ስብዕና የሚፈጠር አዲስ ወንድ እና አዲስ ሴት የለምና እነዚህን ሊፈጥር የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፓፑዋ ኒው ጊኒ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፓፑዋ ኒው ጊኒ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው

በተለይ በቲሞር-ሌስቴ ታሪክ ውስጥ ክርስቲያናዊ መልዕክት ሰብዓዊ እና ማኅበራዊ ዕድገትን የማስተዋወቅ አቅሙ በግልጽ ይታያል። እዚያም ቤተ ክርስቲያን ዘወትር ወደ ሰላም እና እርቅ በመምራት የነጻነት ሂደቷን ከመላው ሕዝብ ጋር ተካፍላለች። ይህም የእምነት ርዕዮተ ዓለም ጉዳይ ሳይሆን ነገር ግን ባሕል፣ ብርሃን፣ ግልጽ እና ከፍ የሚያደርግ የእምነት ጉዳይ ነው። የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት የጠቆሙትን በእምነት እና በባሕል መካከል ያለውን ፍሬያማ ግንኙነት እንደገና የጀመርኩት ለዚህ ነው።

ከምንም በላይ የገረመኝ የሕዝቡ ውበት ነው። ብዙ ችግሮች ቢኖሩትም በትዕግስት ያሳለፈ፣ በመከራ ውስጥ ደስተኛ እና ጥበበኛ መሆኑ ነው። ብዙ ልጆችን የሚወልድ ብቻ ሳይሆን ፈገግታንም የሚያስተምራቸው ሕዝብ ነው። ይህ ለወደፊት ሕይወቱ ዋስትና ነው። ባጭሩ በቲሞር-ሌስቴ የቤተ ክርስቲያንን ወጣትነት አይቻለሁ።ቤተሰቦች፣ ልጆች፣ ወጣቶች፣ በርካታ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች እና የምንኩስናን ሕይወት የሚፈልጉ መኖራቸውን በማየቴ ‘የጸደይ ወቅት አየር’ ተንፍሻለሁ!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቲሞር ሌስቴ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቲሞር ሌስቴ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው

በዚህ ጉዞ የመጨረሻ ሐዋርያዊ ጉብኝቴን ያደረግሁት በሲንጋፖር ነበር። ሲንጋፖር ከሌሎቹ ሦስት አገራት በጣም የተለየች ሀገር ናት። ከተማ-ግዛቷ በጣም ዘመናዊ፣ ለእስያ እና ከዚያም በላይ ለሌሎች አገራት የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ምሰሶ ናት። በሲንጋፖር የክርስቲያኖች ቁጥር ጥቂት ነው። ነገር ግን በተለያዩ ብሔረሰቦች፣ ባሕሎች እና ሃይማኖቶች መካከል ስምምነትን እና ወንድማማችነትን በማፍራት ላይ የምትገኝ ሕያው ቤተ ክርስቲያን ያለባት አገር ናት። በበለጸገች ሲንጋፖር ውስጥ ክርስቲያኖች ጥቂቶች ቢሆኑም ኢኮኖሚያዊ ትርፍ ከሚያረጋግጥላቸው በላይ ወንጌልን ተከትለው የምድር ጨው እና የዓለም ብርሃን የሆኑ ተስፋን የሚመሰክሩ ክርስቲያኖች አሉ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዕለት ሕጻናት ሲባርኩ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዕለት ሕጻናት ሲባርኩ

ይህን ሐዋርያዊ ጉብኝት በስጦታነት የሰጠኝን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ! በእንደዚህ ዓይነት ጉጉት ለተቀበሉኝ የመንግሥት ባለስልጣናት እና ለአገሪቱ አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ ምስጋናዬን ደግሜ አቀርባለሁ። በዚህ ጉብኝት ወቅት ያገኝኋቸውን ሕዝቦች በሙሉ እግዚአብሔር ይባርክ። ወደ ሰላም እና ወደ ወንድማማችነት የሚያደርጉትን ጉዞ እግዚአብሔር ይምራቸዋል!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአዲስ ሙሽሮች ጋር ሰላምታን ሲለዋወጡ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአዲስ ሙሽሮች ጋር ሰላምታን ሲለዋወጡ

 

18 September 2024, 16:55