ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የቤልጂየም ፕሮፌሰሮች አድማሳቸውን በማስፋት እውነትን እንዲፈልጉ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቤልጂየም ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች ጋር በሉቨን የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተገናኝተው ንግግር አድርገዋል። ቅዱስነታቸው ለፕሮፌሰሮች ባደረጉት ንግግር ተመራማሪዎች እውነትን ሳይታክቱ እንዲፈልጉ እና የእውቀት አድማሳቸውን እንዲያሰፉ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቤልጂየም ባደረጉት ሁለተኛ የሐዋርያዊ ጉብኝት ዕለት ከአውሮፓ ኅብረት ዩኒቨርስቲ መምህራን ጋር ለመገናኘት ከብራሰልስ ወጣ ብላ ወደምትገኝ ሉቨን ከተማ የተጓዙ ሲሆን፥ ስብሰባው የተካሄደው ዘንድሮ የምሥረታውን 600ኛ ዓመት በሚያከብረው የሉቨን ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ እንደ ነበር ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለምሁራኑ ባደረጉት ንግግር የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን በሁለገብ ዕውቀት እንዲያንጿቸው እና ተማሪዎችም የዛሬውን ክስተት መተርጎም በመቻል የወደፊቱን እቅድ በማዘጋጀት አስፈላጊነት ላይ አሰላስለዋል። የባህል ምሥረታ መቼም የተገደበ ባለመሆኑ ዩኒቨርስቲዎች የሃሳብ ፍለጋ እና ተነሳሽነት ያካሂዳሉ ብለዋል።

አክለውም “ዩኒቨርሲቲዎች ባሕልንና ሐሳቦችን ማመንጨታቸውን መመልከለቱ ጥሩ ቢሆንም ነገር ግን ከሁሉም በላይ የሰውን ልጅ ዕድገት ለማበረታት እውነትን የመፈለግ ፍቅር ማሳደግ መልካም ነው” ብለው፥ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች ወንጌልን ወደ ሕዝቡ ባሕል በማዳረስ ተልዕኳቸው ውስጥ የዕውቀት አድማሳቸውን በማስፋት የሕይወትን ምንነት የሚገነዘብ እና የሚናገር ወሳኝ መድረክ መፍጠር አለባቸው” ብለዋል።

“የዘመናችን ማኅበረሰብ እውነትን መፈለግ ችላ ያለ፣ ፍላጎቱንም ያጣ ይመስላል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥“ሁሉንም እኩል እና አንጻራዊ ለማድረግ የሚያበቃ መጽናኛን ብቻ ይፈልጋል” ብለዋል። ይህ አተያይ በግል ተወስነን እንድንቀር የሚያደርግ የአእምሮ ድካም እንደሚያስከትል እና በተመሳሳይ መልኩ ምንም ዓይነት ጥያቄ ወደማያቀርብ ቀላል፣ ልፋት የሌለው ምቹ ወደ ሆነ እምነት የመሳብ አደጋ አለው” ሲሉ አክለዋል።

ሊወገድ የሚገባው ሌላ ዓይነት ድንበር፥ ነፍስ የለሽ ምክንያታዊነት እንደሆነ ገልጸው፥ ይህም ሁሉን ነገር በቁሳዊነት እንድንመለከተው በማድረግ የመደነቅ ስሜታችንን እና ችሎታችንን እንደሚያሳጣ ገልጸው፥ አሻግሮ መመልከት መቻል ዓይኖቻችንን ወደ ሰማይ እንድናነሳ፣ ያንን የተደበቀውን እውነት ለማግኘት፣ “ለምንድነው ቆሜ በሕይወት ያለሁት? የሕይወቴ ትርጉም ምንድን ነው?” ለሚሉት እና ለመሳሰሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ይገፋፋናል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዩንቨርሲቲው ፕሮፌሰሮች የምርምር አድማሳቸውን ለማስፋት የሚያስችል የጥበብ ጸጋን ከእግዚአብሔር እንዲጠይቁ በማሳሰብ፥ በ1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 4፡10 ላይ፥ ያቤጽ “እባክህ መባረክን ባርከኝ፥ አገሬንም አስፋው፤ እጅህም ከእኔ ጋር ይሁን፤ እንዳይጎዳኝም ከክፋት ጠብቀኝ” ብሎ የእስራኤልን አምላክ የጠራበትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ ጠቅሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሉቨን የሚገኘው የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ለተሻለ ቤት እና እውነት ፍለጋ ስደተኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ ሲያስተናግድ የነበረውን አቀባበል አወድሰዋል። “እኛ የሚያስፈልገን ድንበሩን የሚያሰፋ እና ራስን ከሌሎች በላይ ከሚያደርግ ባሕል መራቅ ነው” ብለው፥ ዓለማችን ጥሩ እርሾ የገባበት እና ለሰው ልጅ የጋራ ጥቅም አስተዋፅዖ የሚያደርግ ባሕል ያስፈልገዋል ብለዋል።

አቅመ ደካሞችን የሚንከባከብ ሩህሩህ እና ሁሉን አቀፍ ባሕል እንዲገነቡ የዩኒቨርሲቲው መምህራንን በመጋበዝ፥ የብርሃን ጮራን እንዲያውልበልቡ፣ የምርምር አድማሳቸውን እንዲያሰፉ በማሳሰብ፣ ዕረፍት የለሽ የእውነትን ፈላጊዎች እንዲሆኑ፣ የእውቀት ዝግመተኛነት እንዲያሸንፋቸው እና ፍቅራቸውንም እንዲቀንስ አትፍቀዱ” በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሉቨን ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ከፕሮፌሰሮች ጋር ሲሰብሰቡ

 

28 September 2024, 16:34