ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሲንጋፖር ያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት አጠናቀቁ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው በእነዚህ አኅጉራት ውስጥ በሚገኙት አራት አገራት እነርሱም ኢንዶኔዥያ፣ ፓፑዋ ኒው ጊኒ፣ ቲሞር-ሌስቴ እና ሲንጋፖር ውስጥ ያደረጉትን የ12 ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት መፈጸማቸው ታውቋል።
ቅዱስነታቸው በሲንጋፖር ያደረጉትን የመጨረሻ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በማጠቃለል በአገሪቱ የሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 6:25 ደቂቃ ላይ ከከተማው ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተነሱት ሲሆን ወደ ሮም በጣሊያን የሰዓት አቆጣጠር ከማምሻው 12፡25 ላይ እንደሚደርሱ ይጠበቃል።
ቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉባቸው በእነዚህ አራት አገራት ውስጥ በብዙ በሺዎች ለሚቆጠሩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ሕዝቦች ክርስቲያናዊ የተስፋ እና የእምነት መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሲንጋፖር ባደረጉት የመጨረሻው የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ዕለት ከበርካታ የሲንጋፖር ማኅበረሰብ ጋር ውይይቶችን አካሂደዋል።
በቅድሚያ ከአገሪቱ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ከገዳማውያን እና ገዳማው እንዲሁም ከማሌዢያ፣ ከሲንጋፖር እና ከብሩኒ ከመጡ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አባላት ጋር በቅዱስ ፍራንችስኮስ ዛቪየር የሱባኤ ማዕከል ተገናኝተዋል።
ከዚያም በትናንሽ የድሆች እህቶች ገዳማውያት በሚመራው በቅድስት ቴሬዛ የአረጋውያን ማዕከል የሚገኙ በርካታ ተረጂዎችን ጎብኝተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም በሲንጋፖር ካቶሊክ መለስተኛ ኮሌጅ ውስጥ ከልዩ ልዩ ሃይማኖቶች የመጡ ወጣቶችን ባሳተፈ የሃይማኖቶች የጋራ ውይይት ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
ረጅም ጉዞ ያደረጉበት ሐዋርያዊ ጉብኝት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከነሐሴ 27/2016 እስከ መስከረም 3/2017 ዓ. ም. ድረስ በእስያ እና ኦሼኒያ አኅጉራት ባደረጉት 12 የሐዋርያዊ ጉብኝት ቀናት ውስጥ አራት አገራትን እነርሱም ኢንዶኔዥያን፣ ፓፑዋ ኒው ጊኒን፣ ቲሞር-ሌስቴን እና ሲንጋፖርን ለመጎብኘት 7 በረራዎች በማድረግ አሥራ ሁለት ይፋዊ ንግግሮችን በማድረግ አራት ስብከቶችን ማሰማታቸው ታውቋል።
ቅዱስነታቸው የቴሌግራም መልዕክቶችን ልከዋል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሲንጋፖር ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ታርማን ሻንሙጋራትናም በላኩት የቴሌግራም መልዕክት፥ ፕሬዝዳንቱ ላደረጉላቸው ደማቅ የክብር አቀባበል እና ለጋስ መስተንግዶ ምስጋናቸውን አቅርበው፥ ለሀገሪቱ ሰላም፣ አንድነት እና ደህንነት ጸሎት እንደሚያደርጉ አረጋግጠውላቸዋል።