ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የቲሞር-ሌስቴ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን አጠናቀቁ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለማችን ውስጥ ከፍተኛ የካቶሊክ ምዕመናን ቁጥር ከሚገኝባቸው አገራት አንዷ በሆነች ቲሞር-ሌስቴ ያደረጉትን የሦስት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ያጠናቀቁት ረቡዕ መስከረም 1/2017 ዓ. ም. እንደሆነ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቲሞር-ሌስቴ መዲና ዲሊ ባደረጉት የመጨረሻ የሐዋርያዊ ጉብኝት ቀን
ወደ 3,000 ከሚጠጉ ወጣቶች ጋር በስብሰባ ማዕከል ተገናኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
ስለ ነፃነት፣ ስለ ቁርጠኝነት እና የወንድማማችነት እሴቶች አስፈላጊነት ለወጣቶቹ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የቲሞር-ሌስቴ ወጣቶች ነፃነትን ለሌሎች መልካም የማድረጊያ ዕድል አድርገው እንዲወስዱት አሳስበዋል።
ቅዱስነታቸው በፓስፊክ ውቅያኖስ ውስጥ በምትገኝ እና እጅግ ብዙ ካቶሊክ ምዕመናን በሚገኙባት ቲሞር-ሌስቴ ውስጥ የሦስት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት አድርገዋል።
ከ 1.4 ሚሊዮን የቲሞር-ሌስቴ ሕዝብ መካከል ከ 95% በላይ የካቶሊክ እምነት ተከታይ እንደሆነ ሲነገር፥ ከአካባቢው በተገኘ መረጃ መሠረት ወደ 600,000 የሚጠጉ ምዕመናን ማክሰኞ ጳጉሜ 5/2016 ዓ. ም. በዋና ከተማ ዲሊ አቅራቢያ የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ተካፍለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በሲንጋፖር የሦስት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያደርጉ ሲሆን በዚህች አገር ከሚያከናውኗቸው መንፈሳዊ ተገባራት መካከል የመጀመሪያው በአገሪቱ ውስጥ ከሚያገለግሉ የኢሱሳውያን ማኅበር ካኅናት ጋር በግል እንደሚገናኙ ታውቋል።
ቀጥለውም በአገሪቱ ፓርላማ አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተገናኝተው በሲንጋፖር ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ የባሕል ማዕከል ውስጥ ከባለ ሥልጣናት፣ ከሲቪል ማኅበራት ተወካዮች እና ከዲፕሎማሲያዊ አካላት ጋር ተገናኝተው ንግግር እንደሚያደርጉላቸው የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ-ግብር ያመለክታል።