ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መንፈሳዊ ምስል ፊት ቀርበው ጸሎታቸውን ሲያደርሱ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መንፈሳዊ ምስል ፊት ቀርበው ጸሎታቸውን ሲያደርሱ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለ 45ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የቅድስት ድንግል ማርያም ድጋፍ ተማጸኑ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሰኞ ነሐሴ 27/2016 እስከ መስከረም 3/2017 ዓ. ም. በእስያ እና በኦሼኒያ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የቅድስት መንበር መግለጫ ጽሕፈት ቤት ማስታወቁ ይታወሳል። ቅዱስነታቸው ይህን ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝቶችን ከመጀመራቸው አስቀድመው በሮም በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ በመሄድ የሐዋርያዊ ጉዟቸውን አደራ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ 45ኛውን የውጭ አገር ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በማስመልከት እሑድ ነሐሴ 26/2016 ዓ. ም. ጠዋት በሮም የሚገኘውን የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ጎብኝተው፥ የሮም ከተማ ነዋሪዎች ጠባቂ ወደ ሆነች ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መንፈሳዊ ምስል ፊት ቀርበው ጸሎታቸውን አድርሰዋል። ቅዱስነታቸው በጸሎታቸው በኢንዶኔዥያ፣ በፓፑዋ ኒው ጊኒ፣ በቲሞር ሌስቴ እና በሲንጋፖር የሚያደርጉትን የሐዋርያዊ ጉብኝት አደራ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአደራ ሰጥተታል።

ቅዱስነታቸው ጸሎታቸውን ካደረሱ በኋላ ወደ ቫቲካን ተመልሰዋል። ከሰኞ ነሐሴ 27/2016 እስከ መስከረም 3/2017 ዓ. ም. ድረስ በእስያ እና በኦሼኒያ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት እስካሁን ካደረጓቸው ጉብኝቶች መካከል ረጅሙ እንደሚሆን የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።

 

02 September 2024, 09:46