ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሉክሰምበርግ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ሲሰናበቱ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሉክሰምበርግ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ሲሰናበቱ  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሉክሰምበርግ የሚያደርጉትን ጉብኝት ፈጽመው ወደ ቤልጂየም ተጉዘዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮ በአውሮፓ እምብርት በምትገኝ ትንሿ አገር ሉክሰምበርግ ያደረጉትን የስምንት ሰዓት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በፊንደል ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሐሙስ መስከረም 16/2017 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በተደረገላቸው አጭር የስንብት ሥነ-ሥርዓት በማጠናቀቅ የጉብኝታቸው ሁለተኛ አገር ወደ ሆነች ቤልጂየም አቅንተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሉክሰምበርግ ንጉሣዊ ቤተሰብ ልዑል ሄንሪ አልበርት ገብርኤል ፌሊክስ ማይሬ እና ባለቤታቸው ማርያ ቴሬዛ ሜስትሬ ባቲስታ እንዲሁም የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሉክ ፍሬደን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ሐሙስ አመሻሽ ላይ በሉክሰምበርግ አየር ማረፊያ የእንግዳ መቀበያ ውስጥ በግል ተገናኝተው ተወያይተዋል።

ከሉክሰምበርግ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር አጭር ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ በሥነ-ሥርዓቱ መሠረት ወደ አውሮፕላኑ በመጨረሻ ላይ በመግባት በተያዘው የሐዋርያዊ ጉብኝት መርሃ-ግብር መሠረት ወደ ጎረቤት አገር ቤልጂየም ተጉዘዋል።

ከ55 ደቂቃ በረራው በኋላ በብራስልስ ሜልስብሮክ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በአገሪቱ የሰዓት አቆጣጠር ሐሙስ መስከረም 16/2017 ዓ. ም. ከቀኑ 7 ሰዓት ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ደርሰዋል። ቅዱስነታቸው ወደ ብራስልስ ሜልስብሮክ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በቤልጂየም የቅድስት መንበር እንደራሴ ሊቀ ጳጳስ ፍራንኮ ኮፖላ እና በቤልጂየም የቅድስት መንበር አምባሳደር ፓትሪክ ሬኖልት ለቅዱስነታቸው የክብር አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአቀባበል ሥነ-ሥርዓት ከተደረገላቸው በኋላ በቤልጂየም በሚቆዩባቸው ሦስት ቀናት ወደሚያርፉበት ወደ ቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት ተሸኝተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንችስኮስ ከመስከረም 16 እስከ እሑድ መስከረም 19/2017 ዓ. ም. ድረስ በሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም የሚያደርጉትን 46ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት የጀመሩት ትናንት ሐሙስ ሲሆን፥ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ወደ ቫቲካን የሚመለሱትም እሁድ መስከረም 19/2017 ዓ. ም. እንደሆነ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ-ግብር ያመለክታል።

 

27 September 2024, 17:00