ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም ለሚያደርጉት ጉብኝት የእመቤታችንን ድጋፍ ተማጸኑ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም ለሚያደርጉት ጉብኝት የእመቤታችንን ድጋፍ ተማጸኑ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም ለሚያደርጉት ጉብኝት የእመቤታችንን ድጋፍ ተማጸኑ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአውሮፓ አገራት በሆኑት ሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም የሚያደርጉትን 46ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመጀመራቸው ቀደም ብሎ በሮም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቁ ባዚሊካ ሄደው ጸሎት አድርሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ረቡዕ መስከረም 15/2017 ዓ. ም. ማምሻውን ወደ ባዚሊካው በመሄድ ከሐሙስ መስከረም 16 እስከ እሑድ መስከረም 19/2017 ዓ. ም. ድረስ በሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም ለሚያደርጉት 46ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ድጋፍ ለምነዋል።

ቅዱስነታቸው በባዚሊካው ውስጥ በሚገኝ ጥንታዊ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስል ፊት ቀርበው ጸሎት ማድረሳቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል አስታውቋል።

የባዚሊካው አስተዳደር በፌስቡክ ገጹ ላይ ባሠፈረው መልዕክት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተለያዩ አገራት ለሚያደርጓቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ወደ ባዚሊካው ደርሰው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ድጋፍ እና ጥበቃ በጸሎት ሲጠይቁ ይህ 120ኛ ጊዜ መሆኑን አስታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐሙስ መስከረም 16/2017 ዓ. ም. በሚጀምሩት 46ኛ ሐዋርያዊ ጉዞአቸው መጀመሪያ የሚጎበኟት አገር ሉክስንበርግ ስትሆን ቀኑን ሙሉ በዚያ እንደሚያሳልፉ እና በተመሳሳይ ዕለት ምሽቱን ወደ ቤልጂየም መዲና ብራስልስ እንደሚጓዙ እና እዚያው በሚቆዩባቸው ሦስት ቀናት ውስጥ ከቤልጂየም ሕዝብ ጋር እንደሚገናኙ መግለጫው አስታውቋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት በሰጡት አስተያየት፥ “ቅዱስነታቸው በሁለቱ አገራት በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት መጭውን ጊዜ በአብሮነት እና በአስተዋይነት ለመቀጠል ድፍረት የሚሰጥ ነው” ብለው፥ የጉብኝታቸው አንዱ ምክንያት በቤልጂየም የሚገኘው የሉቨን የካቶሊክ ዩኒቨርስቲ 600ኛ ዓመት በዓል ለማክበር እንደሆነም ጠቁመዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአውሮፓ ኅብረት የመሠረት እሴቶቹ ወደ ሆነው የክርስትና እምነት እንዲመለስ ጥሪ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ብጹዕነታቸው ለዜና አገልግሎቱ እንደገለጹት፥ በዩክሬን ውስጥ የሚካሄደውን ጦርነት ጨምሮ በርካታ ቀውሶች ያጋጠሙት የአውሮፓ ኅብረት፥ ያለፈውን እና የወደፊቱን ግንኙነት እንዲያስተካክል ቅድስት መንበር እንደምትረዳው ተናግረዋል።

“በዛሬው ዓለም ተሰሚነት ያለውን ድምጽ እና ስልጣን ለማግኘት ከታሰበ እና አድካሚ የሆኑ ችግሮችን ለማሸነፍ ከተፈለገ አውሮፓ ከብዙ ዓመታት በፊት ያነሳሳውን የእሴቶቹን ታላቅነት እንደገና ማግኘት አለበት” ብለዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በማከልም፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በአውሮፓ ውስጥ ያላትን ሚና በጥልቀት ለማሰላሰል እና እያንዳንዱ ሰው አካሄዱን ከቅዱስ ወንጌል ጋር እንዲያነፃፅር ዕድል ይሰጣል” ብለዋል።

 

26 September 2024, 09:37