ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የሚጸልይ ሕዝብ የወደ ፊት ዕድሉ ሰፊ ነው!” ማለታቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፓፑዋ ኒው ጊኒ ባሳለፉት የመጀመሪያው የሐዋርያዊ ጉብኝት ቀን ከሲቪል ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው ንግግር አድርገዋል። ቅዱስነታቸው ለባለሥልጣናቱ ባደርጉት ንግግር፥ “የሚጸልይ ሕዝብ የወደ ፊት ዕድሉ ሰፊ ነው” ብለው፥ በስምምነት እና በሰላም እንዲኖሩ የተጠሩትን የሀገሪቱን ሕዝቦች ብዝሃነት አወድሰው ለጸሎት አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፓፑዋ ኒው ጊኒ ሐዋርያዊ ጉብኝት በጀመሩበት ቅዳሜ ጳጉሜ 2/2016 ዓ. ም. ማለዳ ከሀገሪቱ ባለስልጣናት፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ከዲፕሎማሲያዊ አካላት ጋር ተገናኝተዋል። የአገሪቱ ርዕሠ መስተዳድር ጄኔራል ፍራንሲስ ቦፌንግ ዳዳ በፖርት ሞርስቢ ቤተ መንግሥት ለቅዱስነታቸው ደማቅ አቀባበል ካደረጉላቸው በኋላ ባሰሙት ንግግር፥ በሀገሪቱ ውስጥ የምትገኝ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እና ለኅብረተሰቡ እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ አስታውሰዋል።


ትልቅ የባህል ሀብት

በመቀጠልም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለባለሥልጣናቱ ባደረጉት ንግግር፥ ፓፑዋ ኒው ጊኒ ከሮም ርቃ የምትገኝ አገር ብትገኝም ለካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ልብ ቅርብ የሆነች ውብ አገር በመሆኗ እና ርዕሠ መስተዳድሩ በሮችዋን ከፍተው ላደረጉላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ደሴቶች ያሉባት፣ ከስምንት መቶ የሚበልጡ ቋንቋዎች የሚነገሩባቸው እና በእያንዳንዱ ደሴት ውስጥ ለሚኖሩ የአገሪቱ ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ያላቸውን ክብር ገልጸው፥ ይህም እጅግ ውብ የባሕል ሃብት መሆኑን ተናግረዋል።

ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የተፈጥሮ ሃብት
አገሪቱ በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገች መሆኗን ያስገነዘቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ምንም እንኳን የውጭ ዕርዳታ ቢያስፈልጋትም የተፈጥሮ ሃብቶቿ ለመላው ማኅበረሰብ ጥቅም ከእግዚአብሔር የተሰጡ ናቸው” ካሉ በኋላ የአካባቢውን ነዋሪዎች የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ተገቢው ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበው፥ እነዚህ ጥረቶች ፍትሃዊ እና ቀጣይነት ባለው መንገድ እንዲከናወኑ ለማድረግ ትልቅ ኃላፊነት እና ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

ውጥረቶችን ማሸነፍ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ የጎሳ ግጭቶች ቆመው የሕዝቡ ሕይወት እንደሚሻሻል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። “ለመላው የሀገሪቱ ሕዝቦች ጥቅም ሲባል ወደ ፍሬያማ ትብብር የሚያመራውን ጎዳና በቆራጥነት እንዲጓዙ” በማለት ጥሪያቸውን አቅርበው፥ ጤና፣ ትምህርት እና የመልካም ሥራ ዕድል እንዲኖር ለማድረግ ቀጣይነት ያለው ውይይት እንደሚረዳ አስረድተዋል ።

ተስፋን እና መንፈሳዊ እሴቶችን ማዳበር
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም፥ “ሁሉም ሰው የሕይወት መሠረታዊ ፍላጎቶችን እንደሚያገኝ እያረጋገጡ ሙሉ እና ትርጉም ያለውን ሕይወት ለመኖር ልቡ ውስጥ ታላቅ ተስፋ ሊኖረው ይገባል” ብለው፥ ለዚህም በእምነት ላይ የተመሠረተ ሰፋ ያለ መንፈሳዊ አመለካከት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

“መንፈሳዊ እሴቶች በምድራዊ ኑሮ ግንባታ እና በሁሉም ጊዜያዊ እውነታዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በሌላ አነጋገር እነዚህ እሴቶች ነፍስን በመንከባከብ እያንዳንዱን የሥራ ውጥኖችን እንደሚያበረታቱ እና እንደሚያጠናክሩ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የፓፑዋ ኒው ጊኒ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው “ጸልዩ” በሚለው በአንድ መሪ ቃል እንደተጠቃለለ በማብራራት፥ “የሚጸልይ ሕዝብ የወደፊት ዕድል እንደሚኖረው፣ ከላይ ጥንካሬን እና ተስፋን እንድሚያገኝ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

በማከልም የጸሎት መንፈስ በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ዓርማ ላይ የገነት ወፍ ምስል እንደመሆኑ መጠን የውስጥ ነፃነትን እንደሚያመጣ፣ በብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማው ላይም የነጻነት ምልክት እንደመሆኑ ሁሉ፥ “ማንም እና ምንም ሊያደናቅፈው የማይችል ነፃነት በውስጣችን አለ፤ ፍቅር የሆነው እግዚአብሔር ልጆቹን ነጻ ለማውጣት እና ለመጠብቅ እንደሚፈልግ አስረድተዋል።

ማኅበረሰቡን የሚጠቅም እምነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀጥለውም፥ የክርስትናን እምነትን የሚከተሉ በርካታ ሕዝቦች ሥርዓቶችን እና መመሪያዎችን ብቻ ከማክበር ባለፈ እንደ ደቀ መዝሙር ኢየሱስ ክርስቶስን በመውደድ እና በመከተል እንደሚታውቁ ያላቸውን ልባዊ ተስፋ ገልጸዋል።

እምነት፥ በተግባር የሚገለጽ ባህል፣ አእምሮን እና ተግባርን የሚያነቃቃ እንዲሁም ወደፊት መንገድን የሚያበራ የብርሃን ፍንጣቂ ሊሆን ይችላል” ብለው፥ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች ህያው የእምነት መግለጫን እና በአገሪቱ ውስጥ እያከናወኑ የሚገኙትን የበጎ አድራጎት ሥራዎች አወድሰው፥ ከሕዝባዊ ተቋማት እና ከሁሉም በጎ ፈቃድ ካላቸው ሰዎች ጋር በትብብር እንዲሠሩ አበረታተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ ከብጹዕ ዮሐንስ ማዙኮኒ ጋር አንጸባራቂ የሆነውን የብፁዕ ፒተር ቶ ሮ ምስክርነት እና ለፓፑዋ ኒው ጊኒ ሕዝብ ብርታት እና ተስፋ ሲሉ ሕይወታቸውን በሙሉ ለአገልግሎት ያዋሉትን ሚስዮናውያንን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፓፑዋ ኒው ጊኒ ሐዋርያዊ ጉብኝት ላይ
07 September 2024, 13:24