ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመካከለኛው እና ምሥራቅ አውሮፓ በጎርፍ የተጎዱትን በጸሎታቸው አስታወሱ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ወቅት ለታዳሚዎች ባደረጉት ንግግር፥ ለአደጋው ተጎጂዎች ያላቸው ቅርበት በመግለጽ በተለይ ሕይወታቸውን ላጡ እና ለቤተሰቦቻቸው እንደሚጸልዩ አረጋግጠዋል።
በአውስትሪያ፣ ሮማኒያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ፖላንድ እና ሌሎች የመካከለኛው እና ምሥራቅ አውሮፓ አገራት የጣለው ከባድ ዝናብ እና በረዶ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱ በትንሹ 21 ሰዎች መሞታቸው ታውቋል።
የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ለአንድ ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጁ ሲሆን፥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የአውሎ ነፋሱ አደጋ ከደረሰባቸው አካባቢዎች ለቀው ወጥተዋል። ከ600,000 በላይ ሕዝብ ያላት የፖላንድ ከተማ ቭሮክላው የጎርፍ መጥለቅለቅ እንደሚኖር ሲጠበቅ የስሎቫኪያ እና የሃንጋሪ ዋና ከተሞች ብራቲስላቫ እና ቡዳፔስት ደግሞ በዳኑቤ ወንዝ ሙላት አደጋ እንዳያጋጥም በማለት የሚተርፉበትን መንገድ እየፈለጉ እንደሚገኙ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ታዳሚዎች ባደረጉት ንግግር፥ የአካባቢው ካቶሊክ ማኅበረሰቦች እና ሌሎች የበጎ ፈቃድ ድርጅቶች ለተቸገሩት እያደረጉ ያለውን ዕርዳታ አወድሰው ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።
ዓለም አቀፍ የአልዛይመር ቀን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተጨማሪም ቅዳሜ መስከረም 11/2017 ዓ. ም. የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የአልዛይመር ቀን በማስታወስ የሕክምና ሳይንስ ለዚህ በሽታ በቅርቡ ፈውስ ማግኘት እንዲችል እና ተገቢ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ በማቅረብ በበሽታው የተጎዱትን እና ቤተሰቦቻቸውን በጸሎት መደገፍ እንደሚገባ አደራ ብለዋል።
ዓለም አቀፍ ቀኑ የአልዛይመር ቀን በዓለም ዙሪያ ከ55 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በሚያጠቃው በዚህ በሽታ እና በሌሎች የአእምሮ ሕመም ዓይነቶች ዙሪያ ያለውን መገለል ለማስወገድ ግንዛቤ ለመስጠት ዓለም አቀፍ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።
ለገዳማውያን እና ገዳማውያቱ ያቀረቡት ሰላምታ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ ታዳሚዎች ሰላምታቸውን አቅርበው በተለይ የማኅበራቸውን ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ ቅዳሜ መስከረም 4/2017 ዓ. ም. ለተመረጡት አዲሱ የቅዱስ ቤነዲክቶስ ማኅበር አለቃ እና ለኮንፌዴሬሽኑ ተወካዮች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የማኅበሩ አባላት በሙሉ በበጎ አድራጎት እና በሚስዮናዊነት ቅንዓት የቅዱስ ቤኔዲክቶስ መንፈስ በዓለም ላይ ይበልጥ ጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ራሳቸውን እንዲያነሳሱ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተጨማሪም ለቀርሜላውያን ባቀረቡት የማበረታቻ ቃላት፥ በጣም ለተቸገሩት ሁልጊዜ የምትደርስ ቤተ ክርስቲያን ምልክት ለመሆን የወንጌል እርሾ እንዲሆኑ አሳስበዋል።