ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከቤልጂየም እና ሉክሰምበርግ ሐዋርያዊ ጉብኝት መልስ ለእመቤታችን ምስጋናን አቀረቡ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከቤልጂየም እና ሉክሰምበርግ ሐዋርያዊ ጉብኝት መልስ ለእመቤታችን ምስጋናን አቀረቡ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቤልጂየም እና ሉክሰምበርግ ላደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ምስጋና አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሁለቱ የአውሮፓ አገራት ሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም ከመስከረም 16-19/2017 ዓ. ም. ድረስ ያደርጉትን 46ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ወደ ሮም ተመልሰዋል። ቅዱስነታቸው ሮም ሲደርሱ ወደ ታላቁ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ድረስ ሄደው ጸሎት ያደረሱ ሲሆን፥ በጉብኝታቸው ወቅት ከጎናቸው በመሆን ለደገፈቻቸው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስጋና አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው እሑድ ዕለት ከፊውሚቺኖ አየር ማረፊያ ወደ ሐዋርያዊ መንበራቸው ሲመለሱ ሮም ውስጥ ወደሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቁ ባዚሊካ ደርሰው የከተማው ነዋሪዎች ጠባቂ በሆነች ቅድስት ድንግል ማርያም ምስል ፊት ጸሎት ማድረሳቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል አስታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስዳት ፍራንችስኮስ በሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም ባደረገው ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት እናታዊ ጥበቃ ላደረገችላቸው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በባዚሊካው በሚገኘው መሠዊያ ፊት የአበባ እቅፍ በማስቀመጥ የምስጋና ጸሎት አድርሰዋል።

ቅዱስነታቸው ከዚያም በመቀጥል ቫቲካን ውስጥ ወደሚገኝ ቅድስት ማርታ የብጹዓው ጳጳሳት መኖሪያቸው መመለሳቸው የቅድስት መንበር መግለጫ አክሎ አስታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ከመጀመራቸው በፊት እና በኋላ ሮማ ከተማ ውስጥ ወደሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያን ታላቁ ባዚሊካን በመሳለም ጸሎት ማቅረባቸው ይታወቃል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህኛው ሐዋርያዊ ጉብኝት ቀደም ብለው ከነሐሴ 27/2016 እስከ መስከረም 3/2017 ዓ. ም. በእስያ እና በኦሼኒያ ባደረጉት የ12 ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አደራን በመስጠት መጀመራቸው እና ከሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መልስም ምስጋናቸውን ካቀረቡላት በኋላ ወደ ሐዋርያዊ መንበራቸው መመለሳቸው ይታወሳል። 

30 September 2024, 11:13