ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ቤልጂየም የሰላም ድልድይ እንድትሆን አውሮፓ እንደምትፈልጋት ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቤልጂየም በማድረግ ላይ በሚገኙት ሐዋርያዊ ግብኝት ከአገሪቱ ሲቪል ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው ንግግር አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው በሉክሰምበርግ ያደረጉትን የአንድ ቀን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ወደ ቤልጂየም የተጓዙት ሐሙስ መስከረም 16/2017 ዓ. ም. እንደሆነ ታውቋል።በቤልጂየም ለባሥልጣናቱ ባደረጉት ንግግርም በ አገሪቱ ቤተ ክኅነት በኩል የተፈጸመውን አሳፋሪ የጾታ ጥቃት አውግዘዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ለሲቪል ባለስልጣናት የሚደረጉትን ንግግር በመቀጠል፥ ቤልጂየም በአውሮፓ አኅጉር እና በብሪታኒያ ደሴቶች መካከል፣ በጀርመንኛ እና ፈረንሳይኛ ተናጋሪ አካባቢዎች መካከል እንዲሁም በደቡብ እና በሰሜን አውሮፓ መካከል ድልድይ ናት” ሲሉ አወድሰው፥ ትንሽ አገር ብትሆንም መግባባትን ለማሰራጨት እና አለመግባባቶች ለማስወገድ የሚያስችል አቅም እንዳላት ተናግረዋል።

“ቤልጂየም የሰላም ድልድይ እንድሆን አውሮፓ ትፈልጋታለች” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ቤልጂየም ረጅም የሕዝቦች እና የባህሎች፣ የካቴድራሎች እና የዩኒቨርሲቲዎች ታሪክ ያላት አገር እንደሆነች በማስታወስ፣ ነገር ግን በሌላ ወገን የጨለማው ጦርነት፣ የቅኝ ግዛት እና የብዝበዛ ታሪክ ያላት አገር እንደሆነችም አስታውሰዋል።

የቤተ ክርስቲያን ሚና

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሲቪል መሪዎች ባደረጉት ንግግር፥ “ሁሉም ሰው ተግዳሮቶችን እና ችግሮችን እንዲጋፈጥ በመርዳት ረገድ መንግሥት የሚጫወተውን ሚና ገልጸው፥ ይህም በከንቱ ግለት ወይም በጨለምተኝነት ተስፋ ሳይሆን በእግዚአብሔር የተወደደው የሰው ልጅ ሊፈርስ እንደማይችል በማመን ነው ብለው፥ የሰው ልጅ ሁልጊዜ ወደ በጎነት እና ወደ ሰላም እንጂ ወደ ከንቱነት አልተጠራንም ብለዋል። ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮዋን ስትፈጽም የአባሎቿን ደካማነት እና ድክመቶች እንዲሁም በታሪክ ውስጥ የሚታዩትን አሳዛኝ እና ያልተገቡ ምስክርነቶችን ማወቅ እንዳለባትም በቅንነት ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተለይ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንቅፋት የሆኑትን በሕጻናት ላይ የተፈጸሙ አሳዛኝ ጾታዊ ጥቃቶችን በማስታወስ ጉዳዩን ለመፍታት ቤተ ክርስቲያን ባላት ቁርጠኝነት ላይ አጽንኦት ሰጥተው፥ ጉዳት የደረሰባቸውን በማዳመጥ እና አብሮአቸው በመሆን እንዲሁም የመከላከል መርሐ-ግብርን በአገሪቱ እና በመላው ዓለም ተግባራዊ ለማድረግ መነሳሳቷን ገልጸዋል። በተጨማሪም በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ የተስፋፋውን የግዳጅ ጉዲፈቻ ልምምድን አስታውሰው፥ ድርጊቱ የሚካሄደው ብዙውን ጊዜ በበጎ ዓላማ እንደ ነበር አስረድተዋል።

በታሪክ ውስጥ የተከሰቱትን እነዚህን እና ሌሎች ክፋቶች በተመለከተ ቤተ ክርስቲያን ግልጽነትን ለማምጣት ሁልጊዜ ጥንካሬን እንደምታገኝ እና የሚበረታው ባሕል የወንጌል እሴቶችን በአንዳንድ የተሳሳቱ መንገዶች ለመጠቀም ቢፈልግም ቤተ ክርስቲያን ፈጽሞ የማትስማማ መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገልጸዋል።

ከታሪክ መማር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሲቪል ባለስልጣናት ያደረጉትን ንግግር ሲያጠቃልሉ፥ “የሀገራት መሪዎች ቤልጅየምን እና ታሪኳን በመመልከት ከዚህ መማር ይችሉ ዘንድ” በሚል ጸሎት አቅርበው፥ የፖለቲካ መሪዎች ለሰላም እንዲሠሩ በመጸለይ፥ የጦርነት አደጋን፣ ውርደትን እና ከንቱነትን እንዴት ማስወገድ እንደሚችሉ ያውቃሉ ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በቤልጂየም ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት መሪ ቃል የሆነውን “ተስፋ” በማስታወስ፥ ተስፋ በሁለተኛነት የሚታይ ሳይሆን ነገር ግን ዘወትር በልባችን ተሸክመን የምንዞረው የእግዚአብሔር ስጦታ እንደሆነ አስረድተዋል።

በመጨረሻም በሕይወት እና በታሪክ ጎዳና ለመጓዝ የሚያስችላቸውን የተስፋ ስጦታን ዘወትር ከመንፈስ ቅዱስ እንዲጠይቁ በማሳሰብ፣ ለባለሥልጣናቱ እና ለቤልጂየም ሕዝቦች በሙሉ መልካምን በመመኘት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአገሪቱ ሲቪል ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው ንግግር ባደረጉበት ወቅት
27 September 2024, 16:50