ወጣቶች በፖላንድ በተዘጋጀ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ (እ.አ.አ 2016) ወጣቶች በፖላንድ በተዘጋጀ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ (እ.አ.አ 2016) 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ወጣቶች በተስፋ ሊመላለሱ እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዓለም ወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት፥ የሕይወት ፈተናዎችን በተስፋ እና በፅናት እንዲቀበሉ አበረታትተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ 39ኛውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በማስመልከት በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ወጣቶች መልዕክት አስተላልፈዋል። “እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁት ይሮጣሉ አይታክቱም” በሚል ርዕሥ የላኩት መልዕክታቸው የሚያተኩረው በነቢዩ ኢሳይያስ ቃላት በመነሳሳት በተስፋ እና በትዕግሥት ጭብጥ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፥ ወጣቶች ሕይወትን እንደ መንፈሳዊ ጉዞ እንዲመለከቱት በማሳሰብ፥ ደስታን ለማግኘት የሚደረግ ጥረት አድካሚ እንደሚሆን አይካድም ብለው፥ ተስፋው ጎልቶ መውጣት ያለበት በዚህ ጉዞ ውስጥ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

እግዚአብሔርን ተስፋቸው የሚያደርጉት አይደክማቸውም

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወጣቶች ከሚገጥሟቸው አንዳንድ ችግሮች አንጻር እንዲጸኑ አበረታትተው፥ “እግዚአብሔርን ተስፋቸው የሚያደርጉት ሳይታክቱ ይጓዛሉ” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። ተስፋ እንዲሁ ተራ ስሜት ብቻ ሳይሆን ንቁ ኃይል እንደሆነ እና ይህም “ወደ ፊት እንድንራመድ የሚፈቅድ ከራሱ ከእግዚአብሔር የተቀበልነው ስጦታ ነው” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሕይወት ትግል ጋር ሊመጣ የሚችል ድካም እንዳለ ተናግረው፥ ይህ ድካም ትርጉም ያለው ጉዞ ለሚያደርጉት ሁሉ የተለመደ መሆኑን በመጠቆም፥ ለእንደዚህ ዓይነቱ ድካም መፍትሄ የሚገኘው በዕረፍት ሳይሆን “የተስፋ ነጋዲያን በመሆን ነው” ብለዋል። በዚህ መልዕክታቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወጣቶች ሕይወትን ሙሉ በሙሉ እንዲቀበሉ ጋብዘው፥ ሰዎች ለመንቀሳቀስ ሳይፈልጉ ዝም ብለው የሚቆሙበት መቀዛቀዝ እንዳይኖር አስጠንቅቀዋል። የቆሙትን ሳይሆን ወደ ፊት የሚጓዙ ሰዎች ድካም ማየት እፈልጋለሁ” ብለዋል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ።

ቅዱስ ቁርባን ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚወስድ መንገድ ነው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የወጣቶችን መንፈሳዊ ጉዞ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው ታሪክ ጋር በማነፃፀር፥ የእስራኤላውያን የምድረ በዳ ጉዞ አስታውሰዋል። በችግር እና በተስፋ መቁረጥ ጊዜ እንኳን እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደማይጥል በማረጋገጥ፥ እንደ አፍቃሪ አባት ለእስራኤላውያን በምድረ በዳ መናን በመስጠት እርሱ ራሱ በሥፍራው በመገኘት እንደመገባቸው አስታውሰዋል። ከዚህ አንጻር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ቅዱስ ቁርባን ወደ ሰማይ የሚወስድ መንገድ መሆኑን በማሳሰብ ወጣቶች የቅዱስ ቁርባንን ጥልቅ ስጦታ እንደገና እንዲገነዘቡት አሳስበዋል።

አገር ጎብኚ ሳይሆን መንፈሳዊ ነጋዲ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳያኑ የ 2025 ዓ. ም. የኢዮቤልዩ በዓልን በማስመልከት መጪው መንፈሳዊ ጉዞ ወጣቶች ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያጠናክሩበት እና ምህረቱን እና ፍቅሩን የሚቀስሙበት አጋጣሚ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ወደ ኢዮቤልዩ የሚደረገው መንፈሳዊ ጉዞ ሥጋዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊም መሆኑን በማሳሰብ፥ ይህን ጉዞ እንደ እውነተኛ የምእመናን ጉዞ እንጂ እንደ አገር ጎበኚዎች ጉዞ ሊወስዱት እንደማይገባ ለወጣቶች በሙሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ ወጣቶች እንዲጎብዙ በማበረታታት፥የጉዟቸውን አደራ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከመቅረባቸው በፊት በጸሎት እንደሚደግፏቸው አረጋግጠው፥ ወጣቶች የእርሷን ምሳሌ በመከተል በጉዟቸው የተስፋ እና የፍቅር ተጓዦች ሆነው መጽናት ይችላሉ በማለት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

17 September 2024, 16:40