ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ቲሞር-ሌስቴ ሲደርሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሰላምታን አቅርበውላቸዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ እስያ እና ኦሽንያ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ሦስተኛ ምዕራፍ በመጀመር ወደ ቲሞር-ሌስቴ መዲና ዲሊ ሲደርሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን ቅዱስነታቸውን በደስታ ተቀብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በፓፑዋ ኒው ጊኒ ያደረጉትን የአራት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ሰኞ ጳጉሜ 4/2016 ዓ. ም. ካቶሊካዊ ምዕመናን በብዛት ወደሚገኙባት ብቸኛዋ አገር ቲሞር-ሌስቴ ተጉዘዋል።

ቅዱስነታቸው ከፓፑዋ ኒው ጊኒ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፖርት ሞርስቢ ተነስተው ሦስት ሰዓት ተኩል ከፈጀ በረራ በኋላ በቲሞር-ሌስቴ ዋና ከተማዋ ዲሊ ወደሚገኝ ፕሬዝዳንት ኒኮላ ሎባቶ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ አውሮፕላን ማረፊያው ሲደርሱ የቲሞር ፕሬዝዳንት ሆሴ ማኑኤል ራሞስ-ሆርታ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዛናና ጉስማኦ ከሌሎች ባለሥልጣናት እና ከ 14 የማዘጋጃ ቤቶች ተወካዮች ጋር በመሆን የክብር አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን፥ ሁለት ልጃገረዶችም ለቅዱስነታቸው ባሕላዊ የቲሞር ቀጭን የአንገት ነጠላ አንገታቸው ላይ አድርገዋል።

ወደ ሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ሲጓዙ ብዙ ሰዎች ደስታቸውን ገልጸዋል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአየር ማረፊያው ተነስተው ዲሊ ውስጥ ወደሚገኘው ሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት የተጓዙ ሲሆን፥ ለቲሞር-ሌስቴ ባለሥልጣናት የመጀመሪያን ይፋዊ ንግግር ለማድረግ ወደ ፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት ከማቅናታቸው በፊት ዕረፍት አድርገዋል። ቅዱስነታቸው ወደ ሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ሲጓዙ ብዙ ሰዎች መንገድ ዳር ቆመው ደስታቸውን እየገለጹ ነጭ እና ቢጫ ቀለማት ያሉባቸውን የቫቲካን ባንዲራዎችን ሲያውለበልቡ ታይተዋል።

ቲሞር-ሌስቴን የጎብኙት ሁለተኛው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 12/1989 ዓ. ም. በኢንዶኔዥያ ወረራ ወቅት ወደዚያ ከተጓዙት ከቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግመኛ ቀጥሎ ቲሞር-ሌስቴን የጎበኙ ሁለተኛው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ሲሆኑ፥ ይህም ከፊል ደሴታማ የእስያ አገር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2002 ነፃነቷን ካገኘች በኋላ የመጀመሪያው እንደሆኑ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቲሞር-ሌስቴ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ማዕከላዊ ጭብጥ፥ “እምነትህ ባህልህ ይሁን” የሚል ሲሆን፥ የቲሞር-ሌስቴ ሕዝቦ ከኢንዶኔዥያ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት ባደረጉት ትግል በቤተ ክርስቲያን ንቁ ድጋፍ ለነበራቸው የቲሞር ሕዝቦች የካቶሊክ እምነት በቀጣይነት ያለውን አስፈላጊነት አጽንዖት ሰጥተዋል።

ቅዱስነታቸው በቲሞር-ሌስቴ ከሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝቶች መካከል ዋናው በጳጉሜ 5/2016 ዓ. ም. በዲሊ ውስጥ የሚያቀርቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሲሆን፥ በዚህ ሥነ-ሥርዓት ላይ ከጎረቤት ኢንዶኔዥያ እና ከአውስትራሊያ የሚመጡ 700,000 ያህል ምዕመናን ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ቅዱስነታቸው እስከ መስከረም 1/2017 ዓ. ም. ድረስ በቲሞር-ሌስቴ በሚኖራቸው ሰፊ የሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት የአካል ጉዳተኛ ልጆችን እንደሚገበኙ፣ ለአገሪቱ ካኅናት ንግግር እንደሚያደርጉ፣ ከኢየሱሳውያን ማኅበር ካኅናት ጋር እንደሚገናኙ እና በጉብኝታቸው የመጨረሻ ቀንም 4,000 ከሚያህሉ የቲሞር ወጣቶች ጋር እንደሚገናኙ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር ያመለክታል።

 

09 September 2024, 17:42