ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በምድራችን ሰላም እንዲወርድ መስከረም 27 ፆም ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት የፈነዳበትን አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ይሆን ዘንድ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም. የጸሎት እና የጾም ቀን ሆኖ እንዲታለፍ ጥሪ አቅርበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ አሁን ያለንበት ዓለም አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ስለምትገኝ ይሄንን ጊዜ ለማለፍ ጸሎት በእጅጉ ስለሚያስፈልግ በርትቶ መጸለይ እንደሚገባ መክረው፥ መጪው መስከረም 27 ሰላም በምድራችን እንዲሰፍን ሁሉም ሰው በጾም እና በጸሎት እንዲያሳልፍ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንቺስኮስ ይሄንን መልዕክት ያስተላለፉት ከመስከረም 22 እስከ ጥቅምት 17 ቀን 2017 ዓ. ም. የሚካሄደውን የቅዱስ ሲኖዶስ ሁለተኛው ዙር መደበኛ ጉባኤን ለማስጀመር በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የመሩት የመክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴ ከተጠናቀቀ በኋላ በስፍራው ለተሰበሰቡ የጉባኤው ተካፋዮች ባደርጉት ንግግር ነው።
በዚህም ንግግራቸው ወቅት ሁሉም የሲኖዶሱ አባላት ከበዓሉ በፊት ባለው ቀን ማለትም መስከረም 26 “ለምድራችን ሰላም እንዲሆን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ልባዊ ጸሎታችንን” ለማቅረብ ሮም በሚገኘው የቅድስት ማርያም ባዝሊካን ከእሳቸው ጋር እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።
በንግግራቸው ወቅት “አብረን እንራመድ” ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ጌታን እንስማው፥ በመንፈስ ቅዱስ ሃይልም እንመራ” በማለት አሳስበዋል።
ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ባህል
በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የጵጵስና ዘመን ለጦር ቀጠናዎች የሚደረጉ የጾም እና የጸሎት ቀናት ቋሚ እና የተለመዱ እንደሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ብጹእነታቸው ከተመረጡ ስድስት ወር ሳይሞላው ማለትም ጳጉሜ 2 ቀን 2005 ዓ.ም. በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ሰብስበው ለሶርያ ሰላም እንዲሆን ጸለየው እንደነበር ይታወሳል።
ከዚህም ሌላ በ 2009 ዓ.ም. ለዲሞክራሳዊት ኮንጎ እና ለደቡብ ሱዳን፣ በ 2012 ዓ.ም. በሊባኖስ በቤሩት ወደብ በደረሰው ፍንዳታ ለተጎዱት ሰዎች፣ እንዲሁም በ 2013 ዓ.ም. ለአፍጋኒስታን የጸሎት እና የጾም ጥሪ አስተላልፈው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ በ 2014 ዓ.ም. በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን ውስጥ በተካሄደው ልብ የሚነካ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ዩክሬን እና ሩሲያ እያደረጉት ያለውን ጦርነት አስመልክተው ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም የምልጃ ጸሎታቸውን ከህዝቡ ጋር አድርሰዋል።