ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የሮም ከተማ ቁስሎችዋን ጥግና አንድነቷን እንድታጠናክር አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሮም ሀገረ ስብከት ውስጥ ለሚገኙ የቁምስና እና ሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች ዓርብ ጥቅምት 15/2017 ዓ. ም. ባደረጉት ንግግር፥ የሮም ማኅበረሰብ እንባን ለመጥረግ እንዲሰበሰብ ጥሪ አቅርበዋል።
የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ካርዲናል ባልዳዛሬ ሬይና ካደረጉት የመክፈቻ ንግግር ቀጥሎ ወደ መንፈስ ቅዱስ ዘንድ በቀረበ ጸሎት የተጀመረው ስብሰባ፥ ቤተ ክርስቲያኗን ከሚያጋጥሟት እንቅፋቶች በላይ በከተማው ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉትን በርካታ ልዩነቶችን ለማስወገድ በከተማዋ ዳርቻዎች የተጀመረው የረዥም ጉዞ ወደ ፍጻሜ መድረሱን እና አዲስ ምዕራፍ መጀመሩን በሚያመለክት፥ “አንድ አድርገን” የሚል መልዕክት ባዚሊካው ውስጥ አስተጋብቷል።
የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች፣ የፖለቲካ እና የሲቪል ማኅበረሰብ መሪዎች
ከ 50 ዓመታት በፊት “ሮምን ያጋጠማት ሕመም” በሚል ርዕሥ በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ የሮም ከተማ ከንቲባ አቶ ሮቤርቶ ጓልቲየሪ፣ የከተማው የፖሊስ ኮሚሽነር፣ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ ተወካይ አቶ አንድሪያ ሪካርዲ እና የማኅበረሰብ ጥናት ተመራማሪ አቶ ጁሴፔ ደ ሪታን ጨምሮ ቁልፍ ፖለቲከኞች ተገኝተዋል።
በስብሰባው ቀዳሚ ሥፍራን ይዘው የተቀመጡት የእምነት ተቋማት ተወካዮች መገኘት በመላው አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን የፍትህ እና የወንድማማችነት ምኞቶችን የሚያሳይ እንደነበር የተመለከተ ሲሆን፥ ከተጋባዦቹ መካከል የአርመን ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ አቡነ ካጃግ ባርሳምያን፣ በሮም የአንግሊካን ማዕከል መሪ ያን ኤርነስት፣ እንዲሁም በሮም የሚገኙ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት መሪዎች ተወካይ ብጹዕ አቡነ ፖሊካርፖስ፣ በጣሊያን የሮማኒያ ኦርቶዶክስ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሚሊታሩ እና ልዩ ልዩ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ተቋማት መሪ አቡነ ሲመዎን ካጽናስ ይገኙበታል።
በጣሊያን የሚገኝ የሙስሊም ማኅበረሰብ ተወካይ ራሚ አልካባላን እና በሶርያ ካቶሊክ ምዕመና የአንጾኪያ ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት ተወካይ፣ በጣሊያን የእስልምና ባሕል ማዕከል ተወካይ አብደላህ ሬዱዋን እና በሮም የታላቁ መስጊድ ተወካይ ተገኝተዋል።
በስብሰባው የቀረቡት ምስክርነቶች
በመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት ሥነ-ሥርዓት ላይ ከነቢዩ ኢሳይያስ እና ከመዝሙረ ዳዊት ምዕ. 34 ተወስደው የተነበቡት ንባባት እግዚአብሔር አምላክ ልባቸው ለተሰበረ እና ለተቸገሩ ሰዎች ያለውን ቅርበት የሚያሳዩ፣ቀጥሎም ከሉቃስ ወንጌል ተወስዶ የተነበበውም፥ እግዚአብሔር ርኅራሄውን የገለጠበት ዓመት የሚገልጽ ሲሆን፥ ከቅዱሳት ንባባቱ በኋላ ልዩ ልዩ ሰዎች የሰጡትን ምስክርነቶች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አዳምጠዋል።
ምስክርነታቸውን ከሰጠቱት መካከል ጋዜጠኛ ማርኮ ዳሚላኖ፥ "የተከፋፈለች ከተማ በእግሯ መቆም አትችልም" ሲል የተናገረው፥ የሮም ከተማን ማኅበራዊ ተግዳሮቶች ክብደት ጠቅለል አድርጎ ያቀረበ እንደ ነበር ተደምጧል። በመቀጠልም የካሪታስ ሮም ዳይሬክተር አቶ ጁስቲኖ ትሪንሲያ ሀገረ ስብከቱ እስከ ስብሰባው ድረስ ያደረገውን ጉዞ የሚያጠቃልል ዘገባ አቅርበው፥ የከተማው አስተዳደር የተቀበለው ኃላፊነት ቀላል እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ቅዱስነታቸው አባላቱ የሰጡትን ምስክርነቶች ካዳመጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፥ የከተማው ማኅብረተሰብ ለድሆች የምሥራቹን ቃል እንዲያደርስ እና በማኅበረሰቡ መካከል የሚገኙ ችግረኞች እንባን በመጥረግ የተስፋ ዘር እንዲዘራ አሳስበዋል።
ድሆች የክርስቶስ ሥጋ ክፍሎች ናቸው
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሮም ከተማን እየደረሱ ባሉ በርካታ ጥልቅ ቁስሎች በማሰላሰል እና በዚህም የተሰማቸውን ሕመም በመግለጽ እንደተናገሩት፥ ጎዳና ላይ የሚኖሩ፣ ሥራ እና መኖሪያ ቤት የሌላቸው ወጣቶች፣ እንክብካቤ የማይደረግላቸው ታማሚ አረጋውያን፣ በልዩ ልዩ ሱሶች እና ሌሎች ‘ዘመናዊ’ ጥገኝነት ውስጥ የወደቁ ወጣቶች፣ በአእምሮ ሕመም የሚሰቃዩ እና ተረስተው ወይም ተስፋ ቆርጠው የሚኖሩ ሰዎች መኖራቸውን በማስታወስ፥ የእነዚህ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን መልክ እና ታሪክ ወደ ልባችን ውስጥ ገብቶ ምን እናድርግ? በታሪካቸው ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስን ስቃይ ይታየናል ወይ? ለጉዳዩ ሃላፊነት መውሰድ እንደሚገባን ይሰማናል ወይ? አብረን ምን እናድርግ? በማለት ጠይቀዋል።
ድህነት፥ ቤተ ክርስቲያን ፈጣን ምላሽ ልትሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ድህነትን የመልዕክታቸው ማዕከል በማድረግ፥ “ድሆች የክርስቶስ ሥጋ” መሆናቸውን በማስታወስ፥ የሚፈለገው የወንጌል መልዕክት ማድረስ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል። ድሆችን በቁጥር ደረጃ ብቻ ማስቀመት እና የማኅበረሰቡ ሸክም አድርጎ መመልከት የማይቻል መሆኑን አበክረው በመናገር፥ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን በስውር የሚያገለግሉ ሰዎች መኖራቸውን ጉባኤውን አስታውሰው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።
በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ደፋር መሆን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምእመናን ሮም ከተማ ውስጥ በሚታዩ በርካታ ችግሮች ምክንያት ተስፋ እንዳይቆርጡ አሳስበው፥ ከተቋማት እና ማህበራት ጋር ቀጣይነት ያለው ውይይት እንዲያደርጉ በማበረታታት፣ በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ድፍረት እንዲኖራቸው፣ የግዴለሽነት ስሜትን ያለ አድልዎ በውይይት እና በትዕግስት በማሸነፍ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ተጨባጭ የተስፋ ሥራዎችን በተግባር ማሳየት
መጪውን የኢዮቤልዩ በዓል ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ምእመናን ተስፋ ሳይቆርጡ ተጨባጭ የተስፋ ሥራዎችን በተግባር እንዲያሳዩ አሳስበው፥ በሮም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመጀመሪያዎቹን ዘሮች የዘራው አባ ሉዊጂ ዲ ሊግሮን እና የእርሱን ፈለግ የተከተሉ በርካታ ምእመናንን አስታውሰዋል።