ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የክርስቲያኖች አንድነት በወንጌል ምስክርነት የታገዘ ሲኖዶሳዊ ጉዞ እንደሆነ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓርብ ጥቅምት 1/2017 ዓ. ም. አመሻሹ ላይ ከልዩ ልዩ የሃይማኖቶ መሪዎች ጋር ሆነው ለክርስቲያኖች አንድነት የሚደረግ ጸሎት የዋዜማ ሥነ-ሥርዓት አክብረዋል። ከዓለም ዙሪያ ከመጡ በሺዎች ከሚቆጠሩ ምዕመናን ጋር በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተፈጸመው ይህ ሥነ-ሥርዓት የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ መታሰቢያ እና አዲስ የክርስቲያኖች አንድነት ጉዞ ዘመን መጀመሪያን ምክንያት በማድረግ እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ጥቅምት 1 ከዛሬ 62 ዓመት በፊት ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ በታላቅ ሥነ-ሥርዓት የተጀመረበት ዕለት መሆኑ ይታወሳል። በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ እንደገለጹት፥ ዛሬ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ፥ “መላው ቤተ ክርስቲያን ወደ ሙሉ የአንድነት ጎዳና እንዲጓዝ ለማድረግ ያለውን ጥልቅ ፍላጎት እና ምስክርነት ለመደገፍ እና አዲስ የክርስቲያኖች አንድነት ዘመን መጀመሪያን ለማክበር የተዘጋጀ ነው” ሲሉ አስረድተል።

የክርስቲያኖች አንድነት እና ሰማዕትነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ የሲኖዶሱ አባቶች በተገኙበት የዋዜማ ሥነ-ሥርዓት ላይ፥ በዮሐ. 17:22 ላይ እንደተጠቀሰው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ “እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ” ያለውን መሠረት ባደረጉ የክርስቲያኖች አንድነት እና ሰማዕትነት ገድል ላይ በማሰላሰል ቃለ ምዕዳናቸውን አሰምተዋል። “እነዚህ ቃላት በተለይ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በመመስከራቸው ምክንያት የእግዚአብሔር ክብር የመጣላቸውን ሰማዕታት የሚመለከቱ ናቸው” ሲሉ ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ሰማዕትነትን የከፈለበት ቦታ ተብሎ በሚታመነው እና በቫቲካን ውስጥ በሚገኝ የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ፊት ለፊት በተካሄደው የዋዜማ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የቀረቡት ጸሎቶች እና አንዳንድ ፅሑፎች ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሠነዶች እና አስተምህሮዎች የተወሰዱ መሆናቸውን ቅዱስነታቸው ገልጸው፥ “ቤተ ክርስቲያንም በሰማዕታቱ ደም ላይ ታነፅታለች” በማለት፥ “ይህም በክርስቲያኖች መካከል ለሚደረገው ዘላቂ የአንድነት ጥሪ ምስክር ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

አንድነትን መልሶ ማምጣት “Unitatis Redintegratio”
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ የክርስቲያኖችን አንድነት በማስመልከት ያስቀመጠውን ድንጋጌ የደነገገውን “Unitatis Redintegratio” ወይም “አንድነትን መልሶ ማምጣት” የሚለውን ሠነድ “ክርስቲያኖች ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀረቡ መጠን እርስ በርሳቸውም እንደሚቀራረቡ ያሳስበናል ብለዋል። በቅዱሳን እና ሰማዕታት ጸሎት የታገዘው ይህ ጥልቅ ትስስር ቤተ ክርስቲያንን በአንድነት ጉዞዋ እንድትጸና አድርጓታል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ለተገኙት የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች እና ልዑካን፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ መክፈቻ ንግግራቸው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻ እራት ላይ ያቀረበው ጸሎት እስኪፈጸም ድረስ ለመጣር ፈልገው ያደረጉትን ንግግር አስታውሰዋል።

አንድነት እና ሲኖዶሳዊነት የጋራ መንገዶች ናቸው
“የክርስቲያኖች አንድነት እና ሲኖዶሳዊነት በጥልቀት የተሳሰሩ ናቸው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሲኖዶሳዊነት እግዚአብሔር ከቤተ ክርስቲያን የሚጠብቀው የሦስተኛው ሺህ ዓመት ጉዞ ነው” ብለዋል። ሲኖዶሳዊ ጉዞ ሁሉም ክርስቲያኖች ሊጓዙት የሚገባ መንገድ እና መሆንም ያለበት ነው” ሲሉ አስረድተው፥ ይህ ጉዞ አዲስ ነገር ለመፍጠር ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ የተሰጠንን የአንድነት ስጦታ ለመቀበል ነው ብለዋል።

“አንድነት ጸጋ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ሲኖዶስ የግኝት ሂደት በመሆኑ፥ የተጠራንበት አንድነት እንዴት ሙሉ በሙሉ እንደሚገለጥ መገመት እንደማንችል ሁሉ፥ “ውጤቱም ምን ሊሆን እንደሚችል አስቀድሞ ማወቅ አንችልም” ብለዋል።

የክርስቲያኖች አንድነት መስማማት እንጂ ወጥነት አይደለም!
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሲኖዶሳዊነት ሂደት በተማሩት ትምህርት ላይ በማሰላሰል እንደተናገሩትም፥ የክርስቲያኖች አንድነት ወጥነት ሳይሆን ነገር ግን መስማማት እንደሆነ ምእመናንን አስታውሰው፥ “አንድነት ለሁሉም ክርስቲያኖች ጥቅም ሲል መንፈስ ቅዱስ ወደ ሕይወት የሚያመጣው እና በብዝሃነት ውስጥ ያለ የመልካም ምግባራት ስምምነት” ነው በማለት አስረድተዋል። ይህ ስምምነት ቅዱስ ባስልዮስ እንደተናገረው ከመንፈስ ቅዱስ እንጂ በሰው ጥረት የሚገኝ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ክርስቲያኖች ወደ አንድነት የሚያደርጉትን ጉዞ ችግሮች እንደማያስቆሙት በመተማመን በፍቅር እና በወንጌል አገልግሎት ወደፊት እንዲራመዱ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል። “በብዝሃነት ውስጥ በስምምነት ወደ አንድነት በሚመራው በመንፈስ ቅዱስ እንታመን” ብለዋል።

ለወንጌል ተልዕኮ ሲባል የሚደረግ አንድነት
ቅዱስነታቸው በክርስቲያናዊ ምስክርነት ላይ በማትኮር ክርስቲያናዊ አንድነት ለተልዕኮ አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበዋል። በዮሐ. 17፡21 ላይ “ሁሉም አንድ እንዲሆኑ፥ . . . ዓለም ያምን ዘንድ” የሚለውን በመጥቀስ፥ በክርስቲያኖች መካከል መለያየት መኖሩ ዓለምን የሚያሳፍር እና የቤተ ክርስቲያንን የወንጌል ተልዕኮ እንደሚጎዳ የጉባኤው አባቶች እንደሚገነዘቡት ገልጸዋል።

ዛሬ በብዙ የዓለማችን ክፍሎች የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ምሳሌ በመከተል ለእምነታቸው ሲሉ ሕይወታቸውን አሳልፈው የሚሰጡ መኖራቸውን ተናግረው፥ የእነዚህ ሰዎች ምስክርነት ከቃላት በላይ እንደሚናገር ገልጸው፥ አንድነት ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል የተወለደ መሆኑን አስታውሰዋል።

መከፋፈልን ለማሸነፍ የቀረበ ጥሪ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቃለ ምዕዳናቸው ማጠቃለያ፥ በመካሄድ ላይ ያለው የሲኖዶስ ጉባኤ የክርስቲያኖችን የጋራ ምስክነት እያደናቀፈ ያለውን መከፋፈል ለማስወገድ ዕድል እንደሚሰጥ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

“ዓለም የጋራ ምስክርነታችንን ይፈልጋል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ እኛም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለጋራ ተልእኳችን ታማኝ እንድንሆን ተጠርተናል ብለዋል። ከተሰቀለው ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ምስል ፊት ተልዕኮውን የተቀበለው የአሲሲው ቅዱስ ፍራንንችስኮስ ክርስቲያኖችን በዕለታዊ ጉዞአቸው ከፍጥረት ሁሉ ጋር ወደ ሙሉ አንድነት እና ስምምነት እንዲመራቸው ጸሎት አቅርበው፥ በመጨረሻም “እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ በማደሩ ተደስቷል፤ በመስቀሉ ደም ሰላም በማድረግ በሰማይም ሆነ በምድር ያሉት ነገሮች ሁሉ በእርሱ ከራሱ ጋር አስታርቋል” (ቆላ 1፡19-20) የሚለውን በመጥቀስ ቃለ ምዕዳናቸውን ደምድመዋል።

 

12 October 2024, 16:19