ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ልጆች ታላቅ የእግዚአብሔር በረከት ናቸው” ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ መስከረም 26/2017 ዓ. ም. ከማር. 10:2-16 ተወስዶ በተነበበው ላይ በማስተንተን ቃለ ምዕዳን አሰምተዋል። እኩለ ቀን ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባሰሙት ስብከት፥ “ልጆች ታላቅ የእግዚአብሔር በረከት ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል። ክቡራት እና ክቡራን የቅዱስነታቸውን ስብከት ሙሉ ትርጉም ከዚህ ቀጥሎ እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞች እና እህቶች መልካም ዕለተ ሰንበት ይሁንላችሁ! በዛሬው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ከማር. 10፡2-16 ተወስዶ የተነበበው የወንጌል ክፍል ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ጋብቻ ፍቅር የተናገረውን ያስታውሰናል። በአንዳንድ አጋጣሚዎች እንዳደረጉት ሁሉ አንዳንድ ፈሪሳውያን ሲከራከሩበት በቆዩት ጉዳይ ላይ ማለትም ባል ከሚስቱ መፋታትን በተመለከተ ጥያቄ አቀረቡለት። ጥያቄውን በማቅረባቸው ወደ ጠብ ሊወስዱት ቢሞክሩም እርሱ ግን አልፈቀደላቸውም። ይልቁንም ትኩረታቸውን ወደ አንድ ይበልጥ አስፈላጊ ወደ ሆነ ውይይት ለመውሰድ ዕድል ስለሰጠው በደስታ ተቀበለ። አስፈላጊው ጉዳይም በወንድ እና በሴት መካከል ያለው የፍቅር ታላቅነት ነው።

በኢየሱስ ክርስቶስ ዘመን ሴት በትዳር ውስጥ የነበረችበት ሁኔታ ከወንዱ ጋር ሲወዳደር ጥሩ አልነበረም። ባል ሚስቱን ሊፈታት እና ወደ ወላጆቿ እንድትመለስ ማድረግ ይችላል። በቅዱሳት መጻሕፍት ሕጋዊ ትርጓሜ ምክንያቶችም ይህ ሊሆን ሊፈጸም ይችላል። ኢየሱስ ክርስቶስም ጠላቶቹን ወደ ፍቅር ጥያቄ መለሳቸው። ሴት እና ወንድ በፈጣሪያቸው ፈቃድ እኩል ክብር ኖሯቸው በልዩነት ውስጥ ተደጋግፈው የሚኖሩ መሆናቸውን ያሳስባቸዋል። በዚህ መንገድ አንዳቸው ለሌላው ረዳት በመሆን ከልብ በመነሳሳት ለዕድገታቸው ፈታኝ የሆኑ ችግሮችን በጋራ ለማሸነፍ ይሞክራሉ (ዘፍ. 2፡20-23)።

ይህ በተግባር እንዲገለጽ ደግሞ የጋራ ስጦታቸው የተሟላ መሆን እንደሚያስፈልግ አጽንዖት ይሰጣል። ይህም የአዲስ ሕይወት መጀመሪያ የሆነው ፍቅር ነው። ስለዚህ ሰው አባቱን እና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣመራል (ዘፍ. 2: 24 እና ማር. 10፡7)። ይህ ታማኝነትን ይጠይቃል፤ በችግር ውስጥ እንኳ ቢሆን እርስ በርስ መከባበርን፣ ታማኝነትን እና ትኅትናን ይጠይቃል (ማር. 10፡15)። አንዳንዴም ግጭት ሲከሰት ለውይይት ክፍት መሆንን ይጠይቃል፤ ሁል ጊዜ ይቅር ባይ መሆንን እና ከሌላው ጋር ለመታረቅ ዝግጁ መሆንን ይጠይቃል። በእርግጥ ይህ ሁሉ ቀላል አይደለም።

እናም እላችኋለሁ፥ ባልና ሚስት ሆይ! የፈለጋችሁትን ያህል ተጣሉ። ነገር ግን በመካከላችሁ ሰላምን ከመፍጠራችሁ በፊት ቀኑ እስኪመሽ አትጠብቁ! ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ምክንያቱም በሚቀጥለው ቀን የሚከሰተው ጦርነት እጅግ አደገኛ ስለሚሆን ነው። ‘አባ እንዴት ሰላም እንፍጠር?’ ብላችሁ ለምታቀርቡት ጥያቄ መልስ የሚሆነው በየዋህነት ልብ በመነሳት “በቃ ሁሉም ይብቃን” ማለት ነው። ነገር ግን በመካከላችሁ ሰላም ሳትፈጥሩ ቀኑ ማለፍ የለበትም።

በተጨማሪም የትዳር ጓደኛሞች ለሕይወት ስጦታ ወይም ለልጅ ስጦታ ክፍት መሆን አስፈላጊ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ልጆች እጅግ ውብ የፍቅር ፍሬ ናቸው። ልጆች በእያንዳንዱ ቤት እና በሁሉም ማኅበረሰብ ውስጥ የእግዚአብሔር ታላቅ በረከት፣ የደስታ እና የተስፋ ምንጭ ናቸው። ልጆች ይኑሯችሁ! ትናንት ከፍተኛ መጽናናትን አግኝቻለሁ። ዕለቱ የቫቲካን ዘብ ጠባቂዎች ቀን ነበር። በዚህ ቀን አንድ ዘብ ጠባቂ ከስምንት ልጆቹ ጋር መጣ! እርሱን ማየት ደስ የሚያሰኝ ነበር። ለሕይወት ክፍት ሁኑ፣ እባካችሁ እግዚአብሔር የሚሰጣችሁን የሕይወት ስጦታ ለመቀበል ዝግጁዎች ሁኑ።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ ሆይ! ፍቅር ዋጋን የሚያስከፍል ቢሆንም ውጤቱ ያማረ ነው። ራሳችንን በፍቅር ውስጥ ለማሳተፍ ፈቃደኞች በሆንን መጠን በውስጡ እውነተኛ ደስታን ይበልጥ እናገኛለን። ስለዚህ እያንዳንዳችን እራሳችንን እንዲህ ብለን እንጠይቅ፥ የእኔ ፍቅሬ እንዴት ነው? ታማኝ ነው? ለጋስ ነው? ጥረት ያደርጋል? ቤተሰቦቻችንስ እንዴት ናቸው? የሕይወት ስጦታ የሆነውን የልጅ ስጦታን ለመቀበል ክፍት ናቸው?

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክርስቲያን ባለትዳሮችን ትርዳቸው። በፖምፔ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ቤተ መቅደስ ውስጥ ከተሰበሰቡት ምእመናን ነጋዲያ ጋር በመቁጠሪያ ጸሎት ወደ እርሷ እንቅረብ።”

 

07 October 2024, 17:16