ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የአብረሃም ቤተሰብ ቤት ከፍተኛ ልዑካንን በቫቲካን ሲቀበሉ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የአብረሃም ቤተሰብ ቤት ከፍተኛ ልዑካንን በቫቲካን ሲቀበሉ  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የአብርሃማዊ ቤተሰብ ቤት ልኡካንን በቫቲካን ተቀብለው አነጋገሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአብርሃማዊ ቤተሰብ ቤት ልዑካንን በቫቲካን ተቀብለው በወንድማማችነት ጎዳና እንዲራመዱ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኞ ጥቅምት 18/2017 ዓ. ም. ከአብርሃማዊ ቤተሰብ ቤት የልዑካን ቡድን ጋር በቫቲካን ተገናኝተው ተነጋግረዋል። የአብርሃማዊ ቤተሰብ ቤት በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዋና ከተማ አቡዳቢ ውስጥ የሚገኝ እና በውስጡ ምኩራብን፣ ቤተ ክርስቲያንን እና መስጊድን የያዘ እንደሆነ ይታወቃል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2023 መጀመሪያ ላይ የተመረቀው ይህ ልዩ ማዕከል በሃይማኖቶች መካከል አብሮነትን እና ስምምነትን የበለጠ በማዳበር የዓለም ሰላም እና አንድነት በማስመልከት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2019 ይፋ የሆነውን የሰብዓዊ ወንድማማችነት ታሪካዊ ሠነድ ዓላማን የሚያበረታታ እንደሆነ ይታወቃል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአብርሃማዊ ቤተሰብ ቤት ፕሬዝዳንት በሆኑት መሐመድ ከሊፋ አል ሙባረክ የተመራው የልዑካን ቡድን የሠነዱን ዓላማ ለማሳካት ላደረገው ጥረት ምስጋናቸውን ያቀረቡለት ሲሆን፥ በቫቲካን የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት ጽሕፈት ቤት ተወካዮችም በቦታው ተገኝተዋል።

የአብርሃማዊ ቤተሰብ ቤት ግንባታ
የአብርሃም ቤተሰብ ቤት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የካቲት ወር 2019 ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ያደረጉትን ታሪካዊ ጉብኝት ተከትሎ የታነጸ እና በሰብዓዊ ወንድማማችነት ሠነድ ላይ የተዘረዘሩ መርሆችን በማካተት፥ ቅዱስነታቸው የአረብ ባሕረ ሰላጤን የጎበኙ የመጀመሪያው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ያደረጋቸው እንደ ሆነ ታውቋል።

አቡ ዳቢ ውስጥ በሳዲያት የባሕል መንደር ውስጥ የሚገኘው የአብርሃም ቤተሰብ ቤት የትምህርት፣ የውይይት እና የእምነት ማዕከል እንደሆነ ሲታወቅ፥ በውስጡ የያዛቸው ሦስቱ የአምልኮ ሥፍራዎች፥ የኢማም አህመድ አል ጣይብ መስጊድ፣ የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ካቶሊካዊ ካቴድራል እና የሙሴ ቤን ማይሞን ምኩራብ እንደሆኑ ይታወቃል።

ማዕከሉ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2023 ከተከፈተ ወዲህ ካቴድራሉ ከ100 በላይ ዝግጅቶችን በማስተባበር በክርስትና ሥርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠር መሠረት እንደ ምስጢረ ተክሊል እና ምስጢረ ጥምቀት ያሉትን ጨምሮ ለሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎቶች እና ጸሎቶች የመጡ 130,000 ምዕመናንን ተቀብሎ አስተናግዷል።

የልዑካን ቡድኑ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እና ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሃይማኖቶች መካከል መግባባትን እና በሰላም አብሮ የመኖር ባሕልን ለማስቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት በማድነቅ በአብርሃም ቤተሰብ ቤት ውስጥ የሚገኘውን የቅዱስ ፍራንችስኮስ ቤተ ክርስቲያን ምሳሌያዊ መግለጫን ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስጦታነት አቅርበዋል።

ሰብዓዊ ወንድማማችነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የካቲት 4/2019 ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በተጓዙበት ወቅት የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሠነድን ከቅዱስነታቸው ጋር በጋራ የፈረሙት በግብጽ የአል-አዛር መስጊድ ታላቁ ኢማም አህመድ አል-ታይብም ጥቅምት 10/2017 ዓ. ም. የአብርሃም ቤተሰብ ቤት ልዑካንን በተመሳሳይ ሁኔታ መቀበላቸው ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰብዓዊ ወንድማማችነትን በማስመልከት፥ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በማለት ይፋ ላደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን መሠረት የሆነው የጋራ ሠነዱ፥ በሁሉም ሰዎች መካከል ሰላም እና መከባበር እንዲኖር ጥሪ ያቀረቡበት፣ በእምነቶች መካከልም ውይይት፣ መከባበር እና ትብብር እንዲኖር ብርታትን የተመኙበት ሠነድ እንደሆነ ይታወቃል።

በአቡ ዳቢ የሚገኘውን የአብርሃማዊ ቤተሰብ ቤት ሦስቱ ዋና ዋና ሃይማኖቶች ማለትም የእስልምና፣ የክርስትና እና የአይሁድ እምነቶች በሰላም አብሮ የመኖር እና የውይይት መገለጫ እንዲሆን ታስቦ የተገነባ ሲሆን፥ በግቢው ውስጥ ሦስት የተለያዩ ነገር ግን በሥነ-ሕንፃ ጥበብ የሚገናኙ የአምልኮ ቦታዎችን እነርሱም መስጊድን፣ ቤተ ክርስቲያንን እና ምኩራብን ያቀፈ እንደሆነ ታውቋል። ከጋራ የማኅበረሰብ ማዕከልነት ጎን ለጎን በሃይማኖቶች መካከል ውይይትን እና መግባባትን ለመፍጠር ያለመ እንዲሁም የትምህርት እና የባህል ማዕከል በመሆን በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል የአንድነት እና የሰላም መልዕክት የሚያበረታቱ ፕሮግራሞችን፣ አውደ ርዕዮችን እና ዝግጅቶችን እንደሚያቀርብ ታውቋል።
 

29 October 2024, 11:28