ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ አደጋ ውስጥ በሚገኝ ዓለማችን ውስጥ ሰላም እንዲወርድ ጸሎት አቀረቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት የፈነዳበት አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ይሆን ዘንድ መስከረም 27/2017 ዓ. ም. የጸሎት እና የጾም ቀን እንዲሆን ጥሪ ማቅረባቸው ሲታወስ፥ በሮም የቅዱስ ሲኖዶስ 16ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ ላይ የሚገኙት የጉባኤው አባላትም እሑድ መስከረም 26/2017 ዓ. ም. በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቁ ባዚሊካ ውስጥ ከእሳቸው ጋር በመተባበር በአደጋ ውስጥ በሚገኝ ዓለም ውስጥ ሰላም እንዲወርድ ጸሎት አቅርበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ ባቀረቡት ጸሎት፥ “ጥላቻን የሚያራግቡ ሰዎች ልብ እንዲለወጥ፣ ሞትን የሚያስከትሉ የጦር መሣሪያዎች ድምጽ ጸጥ እንዲል፣ ዓመፅ ከሰው ልጆች ልብ ውስጥ እንዲጠፋ እና የአገር መሪዎች በሚወስዱት እርምጃ ውስጥ የሰላም ውጥኖችን እንዲይዙ” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።
‘ቅድስት ማርያም፥ የሚያዝኑ ሰዎች እንባ አብሺ!’
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰላም እንዲሰፍን ባቀረቡት ጸሎታቸው፥ በጦርነት ላይ የሚገኙ ሕዝቦች ሐዘን እና ተስፋ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፊት አቅርበዋል። “ዓይኖቻችንን ወደ አንቺ አንስተናል፣ ራሳችንንም ለልብሽ በአደራ እንሰጣለን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ማርያም በምድራዊ ሕይወቷ መከራ ወደ ደረሰባቸው ሰዎች ትቀርብ እንደ ነበር በማስታወስ፥ የሰው ልጅ በአሁኑ ወቅት በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲታመን የሚጠራ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የፍቅር ዕይታ በእጅጉ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።
“በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ በግፍ የተጨቆንነውን እና በጦርነት የምንሞት እኛን ለመርዳት ድረሺልን! በወዳጆቻቸው ሞት ምክንያት የሚያዝኑትን፣ መንገዳችንን ጨለማ ከሚያደርግ ድንዛዜ እንድንነቃ እና ልባችንን ከጥቃት መሣሪያ ነጻ በማድረግ እንባችንን አብሺልን” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል። ከሰላም የሚገኝ ደስታን እና የወንድማማችነት ስሜትን በማጣት ምክንያት ዓለማችን ዛሬ አደጋ ውስጥ እንደሚገኝ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።
የሰው ልጅ ጦርነትን በመተው ሕይወትን እንዲወድ፥ ስቃይ ውስጥ የሚገኙትን፣ ድሆችን፣ አቅም የሌላቸውን፣ሕሙማንን እና ችግረኞችን መንከባከብ እንዲሁም የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከጥፋት መጠበቅን እንዲማር ጸልየው፥ በማጠቃለያቸውም የመቁጠሪያ ጸሎት ንግሥት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ራስ ወዳድነትን እና የክፋት ጥቁር ደመና በማስወገድ በርኅራሄዋ እንድትሞላን በማለት በጸሎታቸው ጠይቀዋል።