ገበሬ ሴቶች በዱባ የተሞሉ ቅርጫቶችን ተሸክመው የጋንግስ ወንዝ ሲያቋርጡ ገበሬ ሴቶች በዱባ የተሞሉ ቅርጫቶችን ተሸክመው የጋንግስ ወንዝ ሲያቋርጡ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የምጣኔ ሃብት መሪዎች የምግብ እጥረት ያለባቸውን ሰዎች እንዲያዳምጡ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዓለም የምግብ ቀንን ምክንያት በማድረግ ለምጣኔ ሃብት መሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል። በሮም በሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና ግብርና ድርጅት ጠቅላይ ጽ/ቤት ለተሰበሰቡት የምጣኔ ሃብት መሪዎች ጥቅምት 6/2017 ዓ. ም. ባስተላለፉት መልዕክት፥ በምግብ ሰንሰለት መጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች ፍላጎት ማዳመጥ እንዳለባቸው አደራ ብለው፥ ለጦር መሣሪያ ግዥ የሚወጣው መዋዕለ ንዋይ ረሃብን ለመዋጋት ቢውል በማለት ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንንችስኮስ ዘንድሮ ጥቅምት 6/2017 ዓ. ም. የተከበረውን የዓለም የምግብ ቀንን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት ሁለት አቅጣጫዎችን በመመልከት ረሃብን ለመዋጋት መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ሲቻል ከፍተኛ ወጪ ለጦር መሣሪያ እና ወታደራዊ ትጥቅ ግንባታ መዋሉን በመቃወም የዓለም መሪዎች በምግብ ሰንሰለቱ መጨረሻ ላይ የሚገኙ ሰዎች ፍላጎቶች እንዲያዳምጡ ጠይቀዋል።

ዘንድሮ ጥቅምት 16 የተከበረውን የዓለም የምግብ ቀን በማስመልከት ዕሮብ ጠዋት በ X ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በጻፉት መልዕክታቸው፥ “ጦርነት በሰው ልጆች መካከል ራስ ወዳድነትን፣ ዓመፅን እና እምነተ ቢስነትን በማምጣት ከፍተኛ ጉዳትን ያስከትላል” ብለዋል።

አክለውም “የጦር መሣሪያ ምርትን የሚደግፍ ማንኛውንም የአመክንዮ መስመር ውድቅ በማድረግ ይልቁንስ ለጦር መሣሪያ እና ወታደራዊ ወጭዎች የሚውለውን ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ረሃብን፣ የጤና እና የትምህርት እጦትን ለመዋጋት ማዋል አለብን” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በየዓመቱ እንደሚያደርጉት፥ በሮም ለሚገኘው የምግብና ግብርና ድርጅት (FAO) ባስተላለፉት የዘንድሮ መልዕክት፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የምጣኔ ሃብት መሪዎች በምግብ ሰንሰለት መጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች፥ እንደ ትናንሽ ገበሬዎች እና በምግብ አቅርቦት ላይ በቀጥታ የሚሳተፉ እንደ ቤተሰብ ያሉ መካከለኛ ማኅበራዊ ቡድኖች ፍላጎት እንዲያዳምጡ አሳስበዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና ግብርና ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቺካ አሬላኖ ለጉባኤው ተሳታፊዎች በንባብ ባሰሙት መልዕክት፥ “ለተሻለ ሕይወት እና መጭው ጊዜ ምግብን የማግኘት መብት” የሚለውን የዘንድሮ የዓለም የምግብ ቀን መሪ ሃሳብ ላይ በማስተንተ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያስተላለፉትን መልዕክት በማስታወስ፥ እያንዳንዱ ሰው አልሚ እና ተመጣጣኝ ምግብ እንዲያገኝ ለማረጋገጥ አብሮነት፣ ፍትህ እና የምግብ ሥርዓት ለውጥ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

“ይህ የሰው ልጅ ከሚያስፈልጉት መሠረታዊ ፍላጎቶች ውስጥ አንዱን የሚያረካ በመሆኑ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው” ብለው፥ እራስን በበቂ የጥራት እና የመጠን ደረጃዎች መሠረት መመገብ ያስፈልጋል” ብለው፥ ይህ ቢሆንም፣ “ብዙውን ጊዜ ይህ መብት ሲገፈፍ ፣ ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ሲተገበር እና ጎጂ መዘዞችን ሲያስከት እናያለን” ብለዋል።

በማኅበረሰቡ የተገለሉ ሰዎች ድምጽ ማዳመጥ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልእክታቸው “በምግብ ሰንሰለት መጨረሻ” ላይ የሚገኙ ሰዎች የበለጠ ትኩረት እንዲሰጣቸው አሳስበዋል። በተለይም የምግብ ፖሊሲዎችን እና መርሃ ግብሮችን በሚነድፉበት ጊዜ እነዚህን ቡድኖች በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ ማሳተፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፥ የሠራተኞች፣ የገበሬዎች፣ የድሆች፣ የተራቡ እና በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ከታች የሚገኙ ሰዎች እውነተኛ ፍላጎቶች ፈጽሞ ሊታለፍ አይገባም” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዓለም መሪዎች ጥረታቸውን በፍትህ እና በወንድማማችነት መምራት እንዳለባቸው በማሳሰብ፥ ይህ የተግባር ጥሪ በኢየሱስ ክርስቶስ የወንጌል ትምህርት፥ እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግና ነቢያትም ይህ ነውና (ማቴ 7፡12) በሚለው ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል።

የምግብ ሥርዓቶችን ማደስ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የምግብ እና ግብርና ድርጅት (FAO) የምግብ ሥርዓትን ለመቀየር የጀመረውን ተነሳሽነት በማድነቅ ወደ ዘላቂነት፣ አካታችነት እና የምግብ ምርት ብዝሃነት እንዲሸጋገር አሳስበዋል። እንዲሁም ሰፋ ያለ ዕይታ እንዲኖር በመጠየቅ ምጣኔ ሃብታዊ እና አካባቢያዊ ብቻ ሳይሆን ራስን የመመገብ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ ገጽታዎች እንዲኖረውም አሳስበዋል።

ዓለም አቀፍ የምግብ ዋስትና ለሁሉም ሰው ጤናማ የአመጋገብ ዘዴን ለማምጣት የምግብ ሥርዓቶች ብዙ እና የተለያዩ ዓይነት ያላቸው አልሚ፣ ተመጣጣኝ፣ ጤናማ እና ዘላቂነት ያላቸው ምግቦች አቅርቦት የማረጋገጥ አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተዋል።

የተቀናጀ ሥነ-ምህዳር እና ሰብዓዊ ክብር
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጠቃሚ ሥነ-ምህዳር አስፈላጊነትን በድጋሚ ገልጸው፥ “የምግብ ቀውስን መፍታት አካባቢን ከመጠበቅ እና የእያንዳንዱን ሰው ክብር ከማስጠበቅ ጋር በተጣጣመ መልኩ መሠራት አለበት” ብለዋል።

“እግዚአብሔር የሰጠን ምድራችን በሰላም አብሮ ለመኖር ክፍት የሆነ የአትክልት ሥፍራ መሆን አለባት” ብለው፥ በረሃብ ላይ እርምጃ መውሰድ ሥነ-ምግባራዊ ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅ ገልጸዋል። “የፍትህ መርሆችን ለድርጊታችን መመሪያ አድርገን ስንወስድ ብቻ የሰዎችን ፍላጎት ማሟላት እንችላለን” ብለዋል።

የቤተ ክርስቲያን ቁርጠኝነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በመልዕክታቸው መጨረሻም፥ ቤተ ክርስቲያን ረሃብን እና ድህነትን ለማጥፋት ያላትን ቁርጠኝነት በማረጋገጥ፥ ቅድስት መንበር ለተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና ግብርና ድርጅት የምትሰጠው ድጋፍ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ እና በሌሎችም ዓለም አቀፋዊ ውጥኖች ላይ ያተኮረ እንደሆነ ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ ሁሉም ሰው በብዛትም ሆነ በጥራት በቂ ምግብ እንዲያገኝ ለማድረግ ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ ማበርከቷን በትጋት እንደምትቀጥ በማረጋገጥ፥ ለዚህ በጎ ተግባር በሚሠሩት ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር በረከት እንዲወርድ ጠይቀዋል።

 

17 October 2024, 17:13