“የቡድን ሰባት አባል አገራት ተወካዮች ስብሰባ ላይ ሆነው “የቡድን ሰባት አባል አገራት ተወካዮች ስብሰባ ላይ ሆነው  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የቡድን ሰባት አባል አገራት መድረክ አንድነትን ለማጠናከር ዕድል ይሰጣል"

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ የሚሲዮናውን ሚናን በማስመልከት ለተዘጋጀ የቡድን ሰባት አባል አገራት የውይይት መድረክ ጥቅምት 13/2017 ዓ. ም. መልዕክት ልከዋል። ቅዱስነታቸው ለውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች በላኩት መልዕክት፥ የቡድን ሰባት አባል አገራት መድረክ አንድነትን ለማጠናከር ዕድል እንደሚሰጥ ገልጸው፥ የስብሰባው ተሳታፊዎች የእርስ በርስ ግንኙነት ባሕልን በጽናት እንዲያሳድጉ በማለት ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በአፍሪካ ልማትን በማስተዋወቅ ላይ ለሚገኝ እና ዘንድሮ ከጥቅምት 13-14/2017 ዓ. ም. ድረስ በጣሊያን ከተማ ፔስካራ ውስጥ ለተዘጋጀ የቡድን ሰባት አባል አገራት የውይይት መድረክ ልባዊ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ከጥቅምት 13 ጀምሮ ለሁለት ቀናት በፔስካራ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው ስብሰባ መሪ ርዕሥ፥ “ትምህርት ለአፍሪካ ልማት እና የሚሲዮናዊያን ሚና” የሚል እንደሆነ ታውቋል። ስብሰባው ጣሊያን በኢንዱስትሪ ከበለጸጉ የቡድን ሰባት አባል አገራት መካከል አንዷ በመሆኗ በፕሬዚደንትነት የምትመራው እና በልማት ላይ ካተኮሩ ተከታታይ ስብሰባዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጣሊያኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ አንቶኒዮ ታያኒ ረቡዕ ጥቅምት 13/2017 ዓ. ም. በላኩት መልዕክት፥ ስብሰባው የድሆችን ሕይወት በልባቸው ውስጥ የያዙ ሰዎች የአብሮነት እና የሰብዓዊ ቁርጠኝነት እሴቶችን እንደሚያጠናክር እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የቅዱስነታቸውን መልዕክት ፈርመው ለስብሰባው ተካፋዮች የላኩት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ሲሆኑ፥ ለስብሰባው ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልዕክታቸው፥ የእርስ በርስ ግንኙነት ባሕልን እንዲያሳድጉ፣ መልካም እና ፍሬያማ ውይይት ለማድረግ ዘወትር ዝግጁ እንዲሆኑ እና የሕያው ወንጌል በጎነት እውነተኛ ምስክሮች እንዲሆኑ” በማለት ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይቶች እና ምስክርነቶች
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት ለስብሰባው ተሳታፊዎች በንባብ ያቀረቡት፥ በጣሊያን መንግሥት የሃይማኖት ነፃነት ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ልዩ መልዕክተኛ አቶ ዳቪዴ ዲዮኒሲ ሲሆኑ፥ ቀጥሎም የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ አንቶኒዮ ታያኒ ንግግር አድርገዋል።

ቀጥሎ በተዘጋጀው የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት በርካታ የጣሊያን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት እንዲሁም ፓኪስታናዊ ፕሮፌሰር ሻሂድ ሞቢን እና በኢየሩሳሌም የቅድስት ሀገር ተንከባካቢ እና የፓትርያርኩ ረዳት አባ ኢብራሂም ፋልታስ ተሳታፊ ሆነዋል። በመቀጠልም በአፍሪካ የትምህርት አገልግሎት ሥራዎችን ከሚያከናውኑ ሚሲዮናዊ ድርጅቶች በኩል ምስክርነቶች ቀርበዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሰኔ ወር በተካሄደው የቡድን ሰባት አባል አገራት ስብሰባ ላይ ንግግር አድርገዋል
ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሰኔ ወር በተካሄደው የቡድን ሰባት አባል አገራት ስብሰባ ላይ ንግግር አድርገዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እና የቡድን ሰባት አባል አገራት
የቡድን ሰባት አባል አገራት ኅብረት በዓለማችን በኤኮኖሚ እጅግ የበለጸጉ የሚባሉ ሰባት አገራትን የሚያሰባስብ ዓለም አቀፍ ድርጅት ሲሆን፥ ጣሊያን በያዝነው 2024 የአውሮፓውያኑ ዓመት ተረኛ ፕሬዚደንት ሆና በማገልግል ላይ እንደምትገኝ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለፉት ዓመታት ውስጥ ለተከናወኑ በርካታ ዝግጅቶች መልዕክት ሲልኩ መቆየታቸው ሲታወስ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያን በሰኔ ወር በተካሄደው የቡድን ሰባት አባል አገራት ስብሰባ ላይ ተገኝተው ንግግር በማድረግ የመጀመሪያው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነዋል።

የሚስዮናውያን ሚናን አስመልክቶ ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር በጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተካሄደውን ስብሰባ የቅድስት መንበር የውጭ ግንኙነት ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በንግግር መክፈታቸው ይታወሳል።

 

24 October 2024, 17:17