ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ በጦርነት ውስጥ "ልጆች እና ቤተሰቦች የመጀመሪያዎቹ ተጠቂዎች ናቸው" አሉ!
የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
"ጦርነት ሁል ጊዜ፣ ሁልጊዜ፣ ሁልጊዜም ሽንፈት ነው" በዚህ ቃል፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጥቅምት 20/2017 ዓ.ም ካደርጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማብቂያ ላይ ባደረጉት ንግግር ቅዱስነታቸው ገልጸዋል፣ በዓለም ዙሪያ ያለው ጦርነት እንዲያበቃ በድጋሚ ተማጽነው ጸሎት አቅርበዋል።
የሰላም ስጦታ ነው
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በሺዎች ለሚቆጠሩት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን ንግግር ሲያደርጉ “ሰማዕቷ ዩክሬን፣ ፍልስጤም፣ እስራኤል፣ ምያንማር፣ ሰሜን ኪቩ እና በጦርነት ውስጥ ያሉ ብዙ አገሮች” በማለት ዓመፅ እና ግጭት የተስፋፋባቸውን አገሮች አስታውሰዋል። በጦርነት ማንም እንደማያሸንፍ ማወቅ ያስፈልጋል እናም “ሰላም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው” በማለት በድጋሚ ተናግሯል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ትናንት 150 ንጹሐን ሰዎች በጥይት ተመተው አይቻለሁ፣ ሕፃናትና ቤተሰቦች ከጦርነት ጋር ምን አገናኛቸው?” ብለዋል። “የመጀመሪያዎቹ ተጠቂዎች እነርሱ መሆናቸው እጅግ በጣም ያሳዝናል" ብለዋል።
ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሰባት “የጅምላ አደጋዎች”
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.አ.አ ከጥቅምት 24 እና 29 መካከል ሰባት "የጅምላ አደጋዎች" መዝግቧል። የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ሰርጥ በስተደቡብ በሚገኘው ማናራ አካባቢ በሚገኙ በርካታ ቤቶች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። 14 ህጻናትን ጨምሮ 33 ሰዎች ተገድለዋል፣ ስድስቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው። በተካሄደው ተከታታይ የአየር ድብደባ 93 የሚደርሱ ፍልስጤማውያን የተፈናቀሉ ሰዎችን በሚኖሩበት የመኖሪያ ህንፃ ውስጥ ተገድለዋል።
አሁንም አገልግሎት እየሰጡ ካሉት ጥቂት ሆስፒታሎች አንዱ በእስራኤል ጦር የተወረረ ሲሆን የጋዛ ሲቪል መከላከያ ከ150 በላይ ሰዎች ውስጥ ተይዘው ታስረዋል ብሏል። በሰሜን የሚገኝ ሌላ ሆስፒታል የእስራኤል ወታደሮች አምቡላንሶችን እና ሌሎች ዕርዳታዎችን ወደ አካባቢው እንዳይገቡ በማቆማቸው የህክምና ቁሳቁስ እና ምግብ ማድረስ ማቆማቸውን ዘግቧል።
እ.አ.አ በጥቅምት 29 የፍልስጤም ሲቪል መከላከያ “ባለፉት 19 ቀናት ውስጥ ብቻ 770 ሰዎች ተገድለዋል” ሲል ዘግቧል።