ለሰላም የቀረበ የመቁጠሪያ ጸሎት የቀረበበት ሥነ-ሥርዓት ለሰላም የቀረበ የመቁጠሪያ ጸሎት የቀረበበት ሥነ-ሥርዓት   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በጦርነት እና በአመጽ ለሚሰቃዩት ሕዝቦች የመቁጠሪያ ጸሎት እንድናደርስ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ረቡዕ መስከረም 29/2017 ዓ. ም. ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ባቀረቡበት ወቅት በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በዩክሬን፣ በምያንማር እና በሱዳን የሚካሄዱ ግጭቶችን በማስታወስ፥ ምእመናን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በተዘጋጀው በዚህ ወር ጸሎታቸውን ወደ እርሷ እንዲያደርሱ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ዕለት ለመላው ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት፥ በዓለም ዙሪያ የሚካሄዱ ጦርነቶች እና ግጭቶች እንዲያበቁ መጸለይ እንደሚገባ የሚያቀርቡትን ጥሪ አድሰዋል። ቅዱስነታቸው ያለፈው እሁድ ሮም ውስጥ በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቁ ባዚሊካ ውስጥ ለሰላም ከተደረገው የመቁጠሪያ ጸሎት በመቀጠል ዛሬ መስከረም 29/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ታዳሚዎች ያቀረቡትን ሳምንታዊ አስተምህሮአቸውን ከመደምደማቸው በፊት በተለመደው በዚህ ወር ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ለሚያቀርቡት ጸሎት ምዕመናን ትኩረት እንዲሰጡ አደራ ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በማሳሰቢያቸው፥ “በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመታመን ሁላችሁም በየቀኑ የመቁጠሪያ ጸሎት እንድናድርስ ካሉ በኋላ በጦርነት መከራ ውስጥ የሚገኙ ሕዝቦች ስቃይ እና የሰላም ተማጽኖን አሳቢ እናት ለሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአደራ እንሰጣለን” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጥላቻ እና በዓመፅ የቆሰሉ አገራት፥ ዩክሬንን፣ ፍልስጤምን፣ እስራኤልን፣ ምያንማርን እና ሱዳንን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው እንደዚሁም የጸሎት ጥሪያቸውን ለጀርመን ምዕመናን ካቀረቡት ሰላምታ ጋር ምዕመናኑ ወደ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ዘንድ በሚያቀርቡት የመቁጠሪያ ጸሎት በኩል ከልጇ ከኢየሱስ ለዓለም ሰላም እና ለቤተ ክርስቲያን አንድነት አብረው እንዲጸልዩ ተማጽነዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም ለፈረንሳይኛ እና አረብኛ ተናጋሪ ምዕመናን ሰላምታቸውን ካቀረቡላቸው በኋላ፥ “ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ጉዞ በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን፥ መንፈስ ቅዱስ የአንድነት እና የሰላም መሣሪያ የመሆን ጸጋን እንዲሰጣቸው እንዲለምኑ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

 

09 October 2024, 17:05