ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጓዳሉፔ እመቤታችን ማርያም በዓል ዕለት መስዋዕተ ቅዳሴን በመሩበት ወቅት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጓዳሉፔ እመቤታችን ማርያም በዓል ዕለት መስዋዕተ ቅዳሴን በመሩበት ወቅት  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከጥቅምት እስከ ታኅሳስ ወር ድረስ የሚመሯቸው መንፈሳዊ በዓላት ይፋ ሆኑ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጥቅምት እስከ ታኅሳስ ወር ድረስ ባሉት ጊዜያት አምስት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓቶችን እንደሚመሩ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የበዓላት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የመንፈሳዊ በዓላት አስተባባሪ ጽ/ቤት እንደገለጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጥቅምት እስከ ታኅሣሥ ወር ድረስ የሚመሯቸው የመንፈሳዊ በዓላት ሥነ-ሥርዓቶች መርሃ ግብርመዘጋጀቱን አስታውቋል።

በወጣው መርሃ ግብር መሠረት የቅዱስነታቸው የመጀመሪያ ተግባር የሚሆነው በያዝነው ዓመት ውስጥ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ብፁዓን ካርዲናሎችን እና ጳጳሳትን በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ማስታወስ ሲሆን፣ ይህም በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ ውስጥ ሰኞ ጥቅምት 25/2017 ዓ. ም. በአገሪቱ የሰዓት አቆጣጠር ከረፋዱ አምስት ሰዓት ላይ የሚፈጸም ይሆናል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ኅዳር 8/2017 ዓ. ም. “የድሆች ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ያቀናል” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የድሆች ቀንን ለስምንተኛ ጊዜ በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት እንደሚያከብሩት እና የቅዱስ ቁርባን ስግደትም ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ እንደሚደረግ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንችስኮስ ባወጁት መሠረት በኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ንጉሥ ክብረ በዓል በሚከበርበት ህዳር 15/2017 ዓ. ም. በሀገረ ስብከት ደረጃ የሚከበረው የዓለም ወጣቶች ቀን የሚከበር ሲሆን፥ ቅዱስነታቸው በዚሁ ዕለት ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የሚጀምረውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓተ እንደሚመሩ ታውቋል።

ቅዱስነታቸው ቅዳሜ ኅዳር 28/2017 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በአሥር ሰዓት በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ ውስጥ ለአዲሶቹ ተሿሚዎች የካርዲናልነት ማዕረግ የሚሰጡበት ይሆናል። በማግሥቱ የላቲን ሥርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠርን በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ዘንድሮ ኅዳር 29/2017 ዓ. ም. የሚከበረውን የጽንሰተ ማርያም ዓመታዊ በዓል ከአዲሶቹ ካርዲናሎች እና የካዲናሎች መማክርት ጋር ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ላይ የሚጀምረውን መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚመሩ ታውቋል።

ቅዱስነታቸው በትውፊት እንደተለመደው በዚሁ ዕለት ከሰዓት በኋላ በአሥር ሰዓት ሮም ውስጥ በፒያሳ ዲ ስፓኛ ወደሚገኝ የጽንሰተ ማርያም መንፈሳዊ ሐውልት ድረስ በመሄድ ጸሎት እንደሚያደርሱ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ታኅሣሥ 3/2017 ዓ. ም. የሚከበረውን የጓዳሉፔ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓል በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ማታ 12 ሰዓት ላይ የሚጀምረውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት የሚመሩ መሆኑን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሥርዓተ አምልኮ አከባበር አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት መርሃ ግብሩን በመጥቀስ አስታውቋል።

 

 

 

 

15 October 2024, 16:06