የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት  (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የጦር መሣሪያን ማንሳት በውይይት ሊተካ ይገባል” ሲሉ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ጥቅምት 24/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው ካደረሱ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በመቀጥል ንግግር አድርገዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባሰሙት ንግግር በጎ ፈቃድ ላላችው ሰዎች በሙሉ ሰላምታ አቅርበው ሳያቋርጡ ለሰላም እንጸልዩ አደራ ብለው፥ በዓለማችን ውስጥ የሚካሄዱ ጦርነቶች በውይይት መፍትሄ እንዲያገኙ ተማጽነዋል።ቅዱስነታቸው በተጨማሪም በምሥራቃዊ ስፔን ቫለንሲያ ክፍለ ሀገር በተከሰተው ከባድ የጎርፍ አደጋ የተጎዱትን ለመርዳት ምእመናን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጦርነትን የሚቃወም የጣሊያን ሕገ መንግሥት አንቀጽ 11 በመጥቀስ ባሰሙት ንግግር፥ በዓለም ዙሪያ በጦርነት ውስጥ የሚገኙት ወገኖች ለውይይት ቅድሚያን በመስጠት ግጭት እንዲያቆሙ ተማጽነዋል። ቅዱስነታቸው ተማጽኖአቸውን ያቀረቡት ሮም ውስጥ ለሚገኝ፣ ጦርነት እና በድህነት ለሚሰቃዩ ዘጠኝ አገራት ዕርዳታን በማድረግ ላይ ለሚገኝ የበጎ አድራጎት ድርጅት አባላት እሁድ ጥቅምት 24/2017 ዓ. ም. ሰላምታቸውን ባቀረቡበት ወቅት እንደ ነበር ታውቋል።

ቅዱስነታቸው የበጎ አድራጎት ድርጅቱ የጣሊያን ሕገ መንግሥት አንቀፅ 11ን እንደሚያከብር ጠቁመው፥ “ጦርነት የሌሎች ሕዝቦች ነፃነት የሚያስከብር እና ዓለም አቀፍ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችል ዘዴ” የሚለውን ጣሊያን እንደምትጻረረው ተናግረዋል። ሁሉም ሕዝቦች ይህን አንቀፅ እንዲያስታውሱ እና በተግባር እንዲያውሉት ያሳሰቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ይህ መርህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንዲሆን፥ ጦርነት ተወግዶ የጦርነት ምክንያቶች በሕግ እና በድርድር እንዲፈቱ፥ የጦር መሣሪያዎችም በውይይት እንዲተኩ” በማለት አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም እንደ ሁል ጊዜው ምዕመናን በጦርነት ለተሰቃዩት ዩክሬን፣ ፍልስጤም፣ እስራኤል፣ ምያንማር እና ሱዳን እንዲጸልዩ ጠይቀዋል።

በስፔን በጎርፍ አደጋ ለተጠቁት ድጋፍ ማድረግ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫሌንሲያ እና በሌሎች የስፔን ክፍለ ሀገራት ውስጥ በተከሰተው ከባድ የጎርፍ አደጋ የሞቱትን በትንሹ 214 ሰዎችን እና የደረሱበት ያልታወቀ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎችን አስታውሰው፥ በአሁኑ ጊዜ በቫሌንሲያ እና ሌሎች የስፔን ግዛቶች ውስጥ በከባድ ስቃይ የወደቁትን ሰዎችን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ምዕመናኑ ለእነዚህ ጉዳተኞች ዕርዳታን በመላክ በጸሎት እንዲያስታውሷቸው አሳስበው፥ በቫሌንሲያ ምሥራቃዊ አካባቢ በጣለው ከባድ ዝናብ በአገሪቱ ታሪክ እጅግ አስከፊ በተባለው የጎርፍ አደጋ ለተጎዱት ሰዎች ያላቸውን ቅርበት ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ቅዳሜ ጥቅምት 23/2017 ዓ. ም. እንደተናገሩት መንግሥት ቀደም ሲል ከተሰማሩት 2,500 የነፍስ አድን ዕርዳታ ከሚያቀርቡ የሠራዊት አባላት በተጨማሪ በፍለጋ እና በጽዳት ሥራ የተሰማሩትን ለመርዳት 5,000 ተጨማሪ የሠራዊት አባላትን ወደ ሥፍራው መላካቸውን የተናገሩ ሲሆን፥ የቫሌንሲያ ክልል ባለስልጣናት ቅዳሜ ጥቅምት 23/2017 ዓ. ም. ምሽት እንዳስታወቁት፥ በክልሉ የሞቱት ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር 211 መድረሱን እና ከእነዚህ መካከል ሁለቱ ከካስቲላ ላ ማንቻ እና አንዱ ከአንዳሉሲያ ግዛት እንደ ነበሩ ገልጸዋል።

 

04 November 2024, 16:22