ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ አማኞች ለኑክሌር ጦርነት በተጋለጠው ዓለም ውስጥ ለሰላም እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ- ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለማችን “በጥላቻ፣ በጠላትነት፣ በጦርነት እና በኒውክሌር ግጭት ስጋት በተከፋፈለ እና ግጭቶች በበዙበት ዓለም” ሁሉም የሰላም አምላክ አማኞች እንዲጸልዩ እና ለውይይት፣ ለእርቅ፣ ለሰላም፣ ለደህንነት እና የሁለንተናዊ ልማት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፣ የሰው ልጆች ሁሉ ሰላም እንዲያገኙ እንዲሰሩ” ጋብዘዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህንን የተናገሩት ረቡዕ ህዳር 11/2017 ዓ.ም ጧት ላይ በሃይማኖት ተቋማት መካከል የሚደርገውን ውይይት በምያሳልጠው የቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እና በኢራን “በሃይማኖቶች እና በባህል መሃከል የሚደረግ ውይይት ማእከል” በተዘጋጀው 12ኛው የጋራ ውይይት ተሳታፊዎችን በቫቲካን በተቀበሉበት ወቅት ነበር።
በውይይቱ ወቅት የተመረጠውን የትምህርት መሪ ሃሳብ በመደገፍ “በጋራ ልናሳየው የምንችለው ለሰላም ያለው ቁርጠኝነት በአለም ፊት እና ከሁሉም በላይ ለመጪው ትውልድ ታማኝ እንድንሆን ያደርገናል” ብለዋል።
የንግግር ባህል
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በሁለቱ አካላት መካከል ያለው የረዥም ጊዜ ትብብር በጋራ ውይይት ስላሳዩት አድናቆታቸውን ገልጸው፣ ወሳኝ የሆነውን የውይይት ባህል የሚያጎለብት መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የቴህራን-ኢስፓሃን ሊቀ ጳጳስ ዶሚኒክ ጆሴፍ ማቲዩ ወደ ካርዲናሎች ኮሌጅ ከፍ እንዲል ለማድረግ መወሰኑን ገልፀው “ለኢራን ቤተክርስቲያን ያላቸውን ቅርበት እና አሳቢነት የሚገልጽ እና በምላሹም መላውን ሰው እና አገራቸውን የምያስከብር" እንደ ሆነም ገልጸዋል።
“በኢራን የምትገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሕይወት፣ ትንሽ መንጋ፣ ከልቤ ጋር በጣም የቀረበ ነው” ያሉት ቅዱስ አባታችን፣ የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች እንደሚገነዘቡ ገልጸው፣ “ስለ ክርስቶስ በመመሥከርና በጸጥታ የበኩሏን አስተዋፅዖ በማበርከት በጽናት ስትቀጥል፥ ነገር ግን ሁሉንም ሃይማኖታዊ፣ ጎሣ ወይም ፖለቲካዊ መድሎዎች ውድቅ በማድረግ ለኅብረተሰቡ በአጠቃላይ ጥቅም ላይ የሚደረገውን ጥረት አጠናክራ እንድትቀጥል ድጋፍ ያስፈልጋታል" ብለዋል።
ቤተሰቡ፡ የመጀመርያው የትምህርት ቦታ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለዚህ ውይይት በተመረጠው ጭብጥ ላይ በማተኮር “የወጣቶች ትምህርት በተለይም በቤተሰብ ውስጥ፡ ለክርስቲያኖችና ለሙስሊሞች ተግዳሮት ነው” የሚል መሪ ቃል እንደ ሆነ የተናገሩት ቅዱስነታቸው “እንዴት የሚያምር ርዕስ ነው! ቤተሰብ፣ የሕይወት መገኛ፣ የመጀመርያው የትምህርት ቦታ ነው” ብለዋል።
"የመጀመሪያውን እርምጃ የምንወስድ እና ሌሎችን ለማዳመጥ፣ እውቅና ለመስጠት እና ለማክበር፣ ለመረዳዳት እና እርስ በርስ ተስማምተን ለመኖር የምንማረው በቤተሰብ ውስጥ ነው" ብሏል።
ከተለያዩ ሃይማኖታዊ ባህሎቻች ውስጥ አንዱ የተለመደ ነገር አረጋውያን ለወጣቶች ትምህርት ያበረከቱት አስተዋፅዖ መሆኑን ጠቁመው አያቶች ለወጣቶች እድገት በዋጋ የማይተመን ምስክርነት እንደሚሰጡ አረጋግጠዋል።
ሃይማኖታዊ ጋብቻ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ክርስቲያኖችም ሆኑ ሙስሊሞች “የተወሳሰቡ የጋብቻ እውነታዎች የአምልኮ ሥርዓቶችን በሚመለከት” የሚወከሉትን የጋራ የትምህርት ፈተና ላይ ብርሃን አበርክተዋል ያሉ ሲሆን በላቲን ቋንቋ አሞሪስ ላቲስያ (ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ) ከተባለው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ በመጥቀስ “እንዲህ ያሉት የቤተሰብ መቼቶች ለሃይማኖታዊ ውይይቶች ልዩ ቦታ እንደሚሰጡ መገንዘብ ቀላል ነው” ብሏል።
በአንዳንድ ማህበረሰቦች ውስጥ ያለው የእምነት መዳከም እና ሃይማኖታዊ ተግባራት በፍጥነት እየተለዋወጠ ባለው ዓለም በተጠቁ ቤተሰቦች ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ እንደሚያሳድር በቁጭት የገለጹት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “የትምህርት ተልእኮውን በተሻለ ሁኔታ ለመወጣት ቤተሰብ የሁሉም ሰው ድጋፍ ያስፈልገዋል። መንግሥትን፣ ትምህርት ቤቱን፣ የሃይማኖት ማኅበረሰቡንና ሌሎች ተቋማትን ጨምሮ' ሲሉ አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል።
ከመላው የሰው ልጅ ቤተሰብ ጋር ይገናኙ
ቅዱስ አባታችን እንዳሉት በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት “ከራሳችን የተለመደ የአስተሳሰብና የተግባር ዘይቤ ለመውጣት እና በትልቁ ሰብዓዊ ቤተሰብ ውስጥ ለመገናኘት ክፍት እንድንሆን ያስችለናል” ብለዋል።
ሆኖም፣ ውይይቱ ፍሬያማ እንዲሆን፣ “ግልጽ፣ ቅን፣ የተከበረ፣ ተግባቢ እና ተጨባጭ መሆን አለበት” ብሏል።
የህሊና እና የሃይማኖት ነፃነት
በመጨረሻም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ወጣቱን ትውልድ ስናስተምር “ለማንኛውም ሰው፣ እያንዳንዱ ማኅበረሰብና እያንዳንዱ ሕዝብ ክብርና መብት ለማስከበር ከመናገርና ከመስራት ፈጽሞ መታከት የለብንም፤” በማለት የኅሊናና የሃይማኖት ነፃነትን እንደ “የመላው የሰብአዊ መብት ግንባታ የማዕዘን ድንጋይ” ነው ሲሉ ቅዱስነታቸው አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል።