ቺሊ እና አርጄንቲና ወደ ጦርነት እንዳይገቡ ያደረገ የሰላም ድርድር 40ኛ ዓመት መታሰቢያ ቺሊ እና አርጄንቲና ወደ ጦርነት እንዳይገቡ ያደረገ የሰላም ድርድር 40ኛ ዓመት መታሰቢያ   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

"ቺሊ እና አርጄንቲና ወደ ጦርነት እንዳይገቡ ያደረገ የሰላም ድርድር 40ኛ ዓመት መታሰቢያ"

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የላቲን አሜሪካ አገራት ቺሊ እና አርጄንቲና ከጦርነት ይልቅ ሰላምን ያስቀደሙበት 40ኛ ዓመት መታሰቢያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በሁለቱ አገራት የሰላም እና የወዳጅነት ስምምነት መታሰቢያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ስምምነቱ የዛሬዎቹን ጦርነቶች ለመፍታት አርአያ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቺሊ እና አርጄንቲና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1978 ወደ ጦርነት አፋፍ ያደረሳቸውን የቢግል ቻናል የድንበር አለመግባባትን አስወግደው አስደናቂ የሰላም እና የወዳጅነት ስምምነት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ኅዳር 29/1984 መፈራረማቸው ይታወሳል።

በሁለቱ የደቡብ አሜሪካ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማረጋጋት የሚረዳውን ስምምነት ቅድስት መንበር ያቀነባበረች ሲሆን የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ግጭቱን በማስታረቅ ረገድ ወሳኝ ሚና መጫወታቸው ይታወሳል።

በቅድስት መንበር የቺሊ እና የአርጀንቲና ኤምባሲዎች ለታሪካዊው የስምምነት ፊርማ መታሰቢያነት ብለው በቫቲካን ሰኞ ኅዳር 16/2017 ዓ. ም. ባዘጋጁት ሥነ-ሥርዓት ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ካርዲናሎች እና ዲፕሎማሲያዊ አካላት ተገኝተዋል።

ለሌሎች ምሳሌ ሊሆን የሚገባ ስምምነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዓለም ሰላም እና ውይይት ዘወትር የሚያቀርቡትን ጥሪ በማደስ ባደረጉት ንግግር፥ “ሁለቱ አገሮች በረዥም እና አስቸጋሪው ድርድር ያሳዩት ጽኑ ቁርጠኝነት፣ የተገኘው የሰላም እና የወዳጅነት ፍሬ ዓለማችን በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ልንጠቀመው የሚገባ አርአያ ሊሆን ይችላል” ብለዋል።

በፍትህ፣ በዓለም አቀፍ ሕግ እና በሰላማዊ መንገድ ላይ ተመሥርቶ ግጭትን በዘላቂነት ለመፍታት የሁለቱ አገራት ሕዝቦች በሚያደርጉት ድጋፍ ከጳጳሳት ጉባኤዎች ጋር በመሆን የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የነበራቸውን ወሳኝ ሚና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውሰው “ዛሬ የኃይል እርምጃ ምን ያህል አሳዛኝ እንደሆነ እንመለከታለን” ሲሉ ተናግረዋል።

ከእግዚአብሔር እና ከጎረቤቶቻችን ጋር የምናደርገው ውይይት እና ወዳጅነት ለሰላም ቁልፍ ናቸው
በሁለቱ የስምምነት ቁልፍ ቃላት ማለትም ሰላም እና ወዳጅነትን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ለችግር ፍፁም እና ሰላማዊ መፍትሄ የሚሆን ይህ አብነት ዛሬ ብዙ ግጭቶች ባሉበት ዓለማችን ውስጥ እንደገና መታየት ያለበት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው፥ ኃይልን መጠቀም እና ማስፈራራት የሰላም ጥረት ውጤታማ እንዳይሆን ማድረጉን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከከባድ የአየር ንብረት ቀውስ እና ከዚህ በፊት ታይቶ ከማያውቅ የሥነ-ሕዝብ ለውጥ ጋር ተዳምሮ የፍትህ መጓደል፣ አመጽ እና የኑሮ አለመመጣጠን ግጭቶች ንዲቀጣጠሉ ማድረጉን አመላክተዋል። ከቁሳዊ ስኬቶች ወይም ከፉክክር ይልቅ ሰብዓዊ ግንኙነቶችን በማስቀደም በልባችን ከእግዚአብሔር ጋር እንድንገናኝ፣ ስለራሳችን፣ ስለጎረቤቶቻችን እና በዙሪያችን ስላሉት እውነታዎች ያለንን ግንዛቤ የበለጠ በማዳበር እነዚህን መሰናክሎች መመከት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው፥ “በሌሎች ግንኙነቶች ውስጥ የሚታየው እና ፈጽሞ የማይጠፋ የደስታ ምንጭ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ወዳጅነት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ የአርጄንቲና እና የቺሊ ጳጳሳት የጋራ ስምምነትን በማስመልከት የሰጡትን መግለጫ የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሁለቱን አገራት ከጦርነት ላዳናቸው እግዚአብሔር ምስጋናቸውን አቅርበው፥ “ሰላምን በሚሹ አገራት መካከል ያለው የእርስ በርስ ግንኙነት እና የስምምነት መንፈስ በላቲን አሜሪካ አኅጉር እና በመላው ዓለም የሚገኙ ድሃ ሕዝቦችን የሚጎዱ በርካታ ማኅበራዊ እና አካባቢያዊ ቀውሶችን ለመፍታት የታቀዱ ተነሳሽነቶችን እና ፖሊሲዎችን ሊያሳድግ እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

መዋዕለ ንዋይን በጦር መሣሪያ ግዥ እያፈሰሱ ስለ ሰላም የማውራት ግብዝነት
በቺሊ እና በአርጄንቲና መካከል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1984 በተደረሰው የሰላም ስምምነት አስፈላጊነት ላይ በማትኮር የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በትዕግስት መደራደር እና መስማማት ጊዜ የማይሽረው ምሳሌ በመሆን ሰላማዊ መፍትሄን ሊያመጣ እንደሚችል እና የሰላም እና የወዳጅነት መንፈስ ተስፋን በማሳየት ዓለም አቀፋዊ ግጭቶችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ተስፋ አድርገዋል።

ከዚሁ ጋር በጦር መሣሪያ ግዥ መዋዕለ ንዋይን እያፈሰሱ ስለ ሰላም የሚናገሩ የበርካታ አገራት “ግብዝነት” ላይ ያላቸውን ምሬት ገልጸው “ይህ ግብዝነት ዘወትር ወደ ወንድማማችነት እና ወደ ሰላም ውድቀት ይመራናል” ብለው፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ውይይትን እንዲያስቀድም እና ሕግንም ሃይሉ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ አርጄንቲናን እና ቺሊ ጨምሮ ሰላምን ለሚጠይቁት አገራት ሁሉ የሰላም ንግሥት የሆነች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት በመለመን የእግዚአብሔርን ቡራኬ ተመኝተውላቸዋል።

 

26 November 2024, 15:53