ፖምፔይ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚገኝ የመቁጠሪያ እመቤታችን ማርያም መንፈሳዊ ምስል ፖምፔይ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚገኝ የመቁጠሪያ እመቤታችን ማርያም መንፈሳዊ ምስል  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ምዕመናን የመቁጠሪያ ጸሎት ጥቅምን በድጋሚ እንዲገነዘቡት አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጣሊያን ፖምፔይ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚገኝ የመቁጠሪያ እመቤታችን ማርያም መንፈሳዊ ምስል 150ኛ ዓመት መታሰቢያን በማስመልከት መልዕክት ልከዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ምዕመናን የመቁጠሪያ ጸሎት ጥቅምን በድጋሚ እንዲገነዘቡት አሳስበው፥ የመቁጠሪያ ጸሎት ለቤተ ክርስቲያን አዲስ የወንጌል አገልግሎት ትልቅ ድጋፍ ማድረግ እንደሚችል በመግለጽ መቁጠሪያ ለሁሉ ሰው ተደራሽ ሊሆን እንደሚችልም አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን ያሳሰቡት በፖምፔይ ከተማ የሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ ጳጳሳዊ ተወካይ ለሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቶማሶ ካቡቶ ቅዳሜ ጥቅምት 30/2017 ዓ. ም. ባስተላለፉት መልዕክት እንደ ነበር ታውቋል።

የፖምፔይ ከተማ ምዕመናን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 የሚከበረውን የኢዮቤልዩ ዓመት በተለያዩ ሐዋርያዊ ተነሳሽነቶች ለማክበር በዝግጅት ላይ ሲሆን በተጨማሪም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚገኘው መንፈስዊ ምስል የተዘጋጀበት 150ኛ ዓመት ለማክበር ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።

የመቁጠሪያ እመቤታችን ማርያም
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክታቸውን ሲጀምሩ እንደገለጹት፥ ይህንን ታላቅ በዓል ከሚያከብሩት ምዕመናን ጋር ያላቸውን መንፈሳዊ ኅብረት ገልጸው፥ የፖምፔይ እመቤታችን ማርያም ቤተ መቅደስን በጸሎት በማስታወስ ወደ የሰማይ እናት ዘንድ በሚያቀርቡት ጸሎት መጽናናትን እና ተስፋን እንደሚያገኙ አስረድተዋል።

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መንፈሳዊ ምስል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ኅዳር 13/1875 ወደ ሥፍራው ከደረሰ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የቤተ መቅደሱ መሥራች የነበረው ጠበቃ ባርቶሎ ሎንጎ በዩኒቨርሲቲው ቆይታ ያጣውን እምነት እንደገና ማግኘቱ ሲታወስ፥ በልቡ በተሰማው ስሜት ከመራራ ተጋድሎ የዳነውም በመቁጠሪያ ጸሎት እንደ ነበር እና “መዳን ከፈግህ የመቁጠሪያ ጸሎት አድርስ” ሲል ከደረሰው መልዕክት ጋር የተገናኘ እንደሆነ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፖምፔይ በቤተ መቅደስ የሚገኝ የእመቤታችን ማርያም መንፈሳዊ ምስል 150ኛ መታሰቢያ በዓል ከመጪው የኢዮቤልዩ ዓመት ጋር የሚገናኝ፣ ተስፋችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያማከለ እና የኒቂያ ጉባኤ 1700 ኛ ዓመት በዓል ሲሆን ይህም በሥላሴ ብርሃን ለመለኮታዊ የኢየሱስ ክርስቶስ የሰውነት ምስጢር ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑን አስታውሰዋል።

የመቁጠሪያ ጸሎት ምንነት እንደገና መገንዘብ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፣ “የመቁጠሪያ ጸሎት ምንነት እንደገና ማወቅ የአዳኙን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ምሥጢር ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ በሚቀርብ ጸሎት በኩል እያሰላሰሉ መመልከት መልካም ነው” ብለዋል።

“መቁጠሪያ ለሁሉም ሰው ተደራሽ ሊሆን የሚችል ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ የተጠራችበትን አዲስ የወንጌል አገልግሎት መደገፍ እንደሚችል ተናግረው፥ በቤተሰብ ውስጥ የመቁጠሪያን ጥቅም እንደገና ማወቅ አስፈላጊ እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ጸሎት ሰላምን ለመገንባት የሚረዳ ብቻ ሳይሆን ወጣቶች የመቁጠሪያ ጸሎትን እንዲያዘወትሩ መምከር አስፈላጊ እንደሆነ ያሳሰቡት ቅዱስነታቸው፥ ወጣቶች የመቁጠሪያ ጸሎትን ተደጋጋሚ እና አሰልቺ አድርገው እንዳይወስዱት ነገር ግን ራስን ለሌሎች ለማቅረብ የማይታክት የፍቅር ተግባር እንደሆነ እንዲገነዘቡት አሳስበዋል።

የመቁጠሪያ ጸሎት የመጽናናት እና የፍቅር ምንጭ ነው
ቅዱስነታቸው በተጨማሪም እንደገለጹት የመቁጠሪያ ጸሎት ለታመሙ እና ለተሰቃዩ ሰዎች የመጽናኛ ምንጭ እንደሆነ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስተሳስረን መልካም መንገድ እንደሆነ እና ድሆችን እና በማኅበረሰቡ የተገለሉትን የሚያቅፍ የፍቅር ሰንሰለት መሆኑንእና ባርቶሎ ሎንጎ በተለይ ወላጅ አልባ በሆኑት እና እስር ቤት ውስጥ በሚገኙ ልጆች መካከል በተግባር ማሳየቱን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ይህን መነሻ በማድረግ የእመቤታችን ማርያም መንፈሳዊ ምስል 150ኛ መታሰቢያ በዓልን የሚያከብሩት ምዕምናን በቤተ መቅደሱ ዙሪያ በሚያደረጉት በርካታ ሐዋርያዊ ተነሳሽነቶች የጀመሩትን ታላቅ የበጎ አድራጎት ተግባራትን በአዲስ ስሜት እንዲቀጥሉ ብርታትን በመመኘት የመቁጠሪያ ጸሎት የቤተ መቅደሱ መሥራች ብፁዕ ባርቶሎ ሎንጎ ትቶልን የሄደው እጅግ ውብ መንፈሳዊ ቅርስ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ለዘመኑ ሰው መመስከር
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም፥ በፖምፔይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መልዕክት አማካይነት እግዚአብሔር የወንድማማችነትን ጎዳና እንደገና ማግኘት ለሚፈልግ የሰው ልጅ መናገሩን እንዲቀጥል ጸሎት አቅርበዋል።

ቅዱስነታቸው በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ ተበታትነው የሚገኙ በርካታ ምእመናን ከወንድሞቻቸው እና ከእህቶቻቸው ጋር በተለይም እጅግ ከተቸገሩት ሰዎች ጋር ያላቸውን ቅርርብ በመመስከር ሁልጊዜ ከጌታ ጋር በታማኝነት እንደሚጸኑ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

 

11 November 2024, 15:10