ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ "ጦርነት የጭንቀት ምንጭ እና የጨለማ ጊዜ ማስታወሻ ነው" አሉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2018 በኢስቶኒያ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ወቅታዊ ሁኔታዎችን እና ዛሬ አውሮፓ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በመመልከትም የከባድ ጭንቀት ምንጭ እና ያለፈውን የጨለማ ጊዜ የሚያሳዝን ሁኔታ የሚያስተጋባ ነው” በማለት የአገሪቱን ካቶሊክ ምዕመናንን አሳስበዋል። ኢስቶኒያ በሰላም፣ በፍትህ፣ በአብሮነት እና በእያንዳንዱ ሰው ክብር ላይ የተመሠረተ ማኅበረሰብን ለመገንባት እና እንደዚሁም ለእግዚአብሔር የተስፋ ቃል የተባበረ ምስክርነት ለመስጠት ከሌሎች የክርስትና እምነት ተከታዮች ጋር የበለጠ መተባበር እንደሚገባ አሳስበዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለታሊን ከተማ ጳጳስ አቡነ ፊሊፕ ጆርዳን በላኩት መልዕክት የኢስቶኒያ ሐዋርያዊ አስተዳደር የተመሠረተበትን መቶኛ ዓመት እና በቅርቡ ወደ ሀገረ ስብከት ደረጃ ማደጓን በምሥራቅ አውሮፓ አገራት ለሚገኙት ምዕመናን አስታውሰዋል።
ለእምነት ታማኝ መሆን
የሐዋርያዊ አስተዳደር ምሥረታ መቶኛ ዓመት መታሰቢያ በዓሉ በአገሪቷ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ይህች ትንሽ ነገር ግን ንቁ የሆነች ቤተ ክርስቲያን የርህራሄ እና በመላ አገሪቱ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወንዶችና ሴቶች የመንፈሳዊ ምግብ ምንጭ እንድትሆን ያስቻለ እና በመቶ ዓመታት ውስጥ ለካቶሊክ እምነት ጠንካራ ታማኝነት የታየበት ሂደት የሚከበርበት ነው” ብለዋል። በተመሳሳይም የምሥረታው መቶኛ ዓመት በዓል ምዕመናን በእግዚአብሔር ላይ ያለውን የማይናወጥ ተስፋ እና እምነት፣ የብዙ አሥርተ ዓመታት የግዞት ስቃይ እና ጭቆናን የሚያስታውስ ነው” ብለዋል።
የሊቀ ጳጳስ አቡነ ፕሮፋይትሊች ምስክርነት
ያለፈውን ምዕተ-ዓመት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “በኢስቶኒያ ለሚገኘው ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ ሐዋርያዊ አገልግሎትን ለመስጠት እና ለመደገፍ ጥረት ያደረጉ ቆራጥ እና ደፋር የቀድሞው አባቶች ላሳዩት የእምነት ምሳሌ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በዜግነት ጀርመናዊ ሆነው በኢስቶኒያ ያደጉት የኢስቶኒያ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ እና የእግዚአብሔር አገልጋይ የነበሩ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤድዋርድ ፕሮፋይትሊችን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ በሶቪየት አገዛዝ የስደት ሰለባ እንደ ነበሩ ጠቅሰው፥ የእርሳቸው ምስክርነት እና የመንፈስ ጥንካሬ ለመንጋው ቅርብ ሆነው ደማቸውን እስከ ማፍሰስ እንዳደረሳቸው እና እስከ ዛሬ ድረስ ፍሬ እያፈራ ያለውን ዘር እንዲዘሩ ማድረጉን በመልዕክታቸው ላይ ገልጸዋል።
በወጣቶች መካከል ወንጌልን ለመስበክ ያለው ቅንዓት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም፥ ሀገረ ስብከቱን ልዩ የሚያደርገው አስደናቂ የእምነት እና የበጎ ሥራ ውርስ አሁን ያለው የካህናት፣ የገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም የምእመናን ወገን ወደፊት እየተጓዘ አስደሳች ሚስዮናዊ ደቀ መዝሙርነት እንዲያድግ የሚያበረታታ ነው” ብለዋል። በእርግጥ የምሥረታው መቶኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል “ኢስቶኒያ ውስጥ ለመንፈሳዊ መታደስ አጋጣሚ እንደሚሆን፣ በተለይ በወጣቶች መካከል አዲስ የወንጌል ምስክርነት እገልግሎት እንዲሰፍን እና ወንጌልን በብቃት ማወጅ የእግዚአብሔርን ፍቅር፣ ምሕረት እና እርቅ መመስከር እንዲችሉ የሚያደርግ ነው” ብለው፥ በዚህም የኢየሱስ ክርስቶስን ብርሃን እና የወንጌልን የነጻነት ኃይል በእግዚአብሔር ለማያምኑ ብዙ ሰዎች ማምጣት እንደሚችሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ለስደተኞች የድጋፍ እጅን መዘርጋት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ላይ፥ የኢስቶኒያ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ዕርዳታ ዘወትር በመታመን እና ጉልህ ምልክት በመሆን፥ በጎ ፈቃድ ካላቸው ሰዎች ሁሉ ጋር ለስደተኞች እና ተጋላጭ ለሆኑት ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የወዳጅነት እጅን ለመዘርጋት መንፈስ ቅዱስ እንደሚያግዛቸው ተናግረው፥ እግዚአብሔር ከቤተ ክኅነት፣ ከገዳማውያት እና ገዳማውያን እንዲሁም በኢስቶኒያ በምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምእመናን በእምነት፣ በተስፋ እና በፍቅር የተሞላውን ቀጣዩን የጉዞ ምዕራፍ ለመጀመር የሚያስች ኃይል እንዲሰጥ መጸለይ እንደሚገባ በማሳሰብ መልዕክታቸውን ደምድመዋል።