ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት በሞት የተለዩ ካርዲናሎችን እና ጳጳሳትን በጸሎት አስታወሱ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት በሞት የተለዩ ካርዲናሎችን እና ጳጳሳትን በጸሎት አስታወሱ   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በዘንድሮው የአውሮፓውያኑ ዓመት ያረፉትን ካርዲናሎች እና ጳጳሳት በጸሎት አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለፉት አሥራ ሁለት ወራት ውስጥ ላረፉት ብጹዓን ካርዲናሎች እና ጳጳሳት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አቅርበው፥ እነርሱን ለማስታወስ የቀረበው መስዋዕተ ቅዳሴ በስማቸው የቀረበ የምልጃ ጸሎት መሆኑን አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በያዝነው ዓመት በሞት የተለዩ ሰባት ካርዲናሎችን እና ከ120 በላይ የሚሆኑ ጳጳሳትን ለማስታወስ ሰኞ ጥቅምት 25/2017 ዓ. ም. ጠዋት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ባሰሙት ስብከት፥ ከኢየሱስ ጋር የተሰቀለው ሌባ፥ “ኢየሱስ ሆይ! በመንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ” (ሉቃ. 23:42) ባለው ላይ አሰላስለዋል።

ሌባው ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ ሳይሆን ነገር ግን ኢየሱስን በሕይወቱ መጨረሻ ላይ ያገኘ ወንጀለኛ እንደ ነበር አስረድተው፥ “በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰው የዚህ ሰው የመጨረሻ ቃል በእውነት የተሞላ ውይይት ለመጀመር ያግዛል” ብለዋል።

“ለሠራው የሚገባውን ሽልማት ከተቀበለ ወንጀለኛ ጋር ማመሳሰል እንችላለን” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ይልቁንም ይበልጥ አስፈላጊ የሚሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያስበን በማስታወስ ከወንጀለኛው ጋር መሆን እንችላለን” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ማታወስ” በሚለው ላይ እንዲያሰላስሉ ምእመናንን ጋብዘው፥ ማስታወስ የሚለው ቃል ወደ ጣሊያንኛ ሲተረጎም፥ “በልብ ውስጥ መያዝ” ማለት እንደ ሆነ አስረድተዋል። ምንም እንኳን ወንጀለኛው የሚቀበል ልብ ብቻ ለማግኘት የፈለገ ሲሆን፥ ባለቀ ሰዓት ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢአተኛውን ጸሎት መስማቱን ተናግረዋል።

“በኢየሱስ ክርስቶስ መታወስ በምሕረት የተሞላ ስለሆነ ዘወትር ውጤታማ ነው” በማለት አጥብቀው የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ስለ እግዚአብሔር ልብ ሲናገሩ፥ ሰዎች በዘመናት ሁሉ ከእግዚአብሔር ልብ ውስጥ የመዳን ተስፋን ሊያገኙ ይችላሉ” ሲሉ አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው በማጠቃለያ ኢየሱስ ሩህሩህ እና መሐሪ ዳኛ መሆኑን በመግለጽ በተለይ ባለፉት አሥራ ሁለት ወራት ውስጥ በሞት የተለዩ ጳጳሳትን እና ካርዲናሎችን በማስታወስ፥ የመታሰቢያው መስዋዕተ ቅዳሴ የምልጃ ጸሎት እንደሚሆንላቸው እና “ከእነርሱ ጋር በሰማይ ለመደሰት በጽኑ ተስፋ በጉጉት እንጠባበቃለን” በማለት ስብከታቸውን ደምድመዋል።

 

04 November 2024, 16:28