ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ልጆቻቸውን በሞት ያጡ ወላጆችን በጸሎት አስታወሱ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቪዲዮ መገናኛ አማካይነት ባስተላለፉት መልዕክቱት ልጆቻቸውን በሞት ያጡ ወላ ሊያጽናና የሚችል ምንም ዓይነት ቃላት የሉም ብለው፥ ምንም እንኳን የትዳር ጓደኞቻቸውን ወይም ወላጆችን ያጡ ሰዎችን ማጽናና ቢቻልም ነገር ግን ልጆቻቸውን በሞት ያጡትን በምንም ዓይነት ቃላት ማጽናናት እንደማይቻል ገልጸዋል።
የማጽናኛ ሙከራዎች እና ቃላት ስሜታዊ ሊመስሉ እንደሚችሉ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ምንም እንኳን ለጥሩ ዓላማ ቢሆንም ቁስሉን ሊያባብሰው እንደሚችል ተናግረው፥ ይልቁንም ልጃቸውን በሞት ያጡ ወላጆችን በፍቅር ልንቀርባቸው እና የሚሰማቸውን ሥቃይ በኃላፊነት ልንጠነቀቅላቸው እንደሚገባ በማሳሰብ ኢየሱስ ክርስቶስ ያዘኑትን ለማጽናናት የተጠቀማቸውን መንገዶች መከተል እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
በተጨማሪም በእምነት የተደገፉ ወላጆች ተመሳሳይ ችግር ላጋጠማቸው እና በተስፋ ዳግመኛ ለተወለዱት ሰዎች ሐዘናቸውን በማካፈል መጽናናትን ሊያገኙ እንደሚችሉም ተናግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለኅዳር ወር ያዘጋጁት የጸሎት ሐሳብ ልጆቻቸውን በሞት ያጡ ወላጆች ድጋፍን ከማኅበረሰባቸው እንዲያገኙ እና መጽናናትን በማግኘት የልብ ሰላምን እንዲያገኙ የሚያበረታታ እንደሆነ ተመልክቷል።