ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሕንድ የማላንካራ ማር ቶማ የሶርያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር በቫቲካን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሕንድ የማላንካራ ማር ቶማ የሶርያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር በቫቲካን   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ሲኖዶሳዊነት እና የክርስቲያኖች አንድነት የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሕንድ የማላንካራ ማር ቶማ የሶርያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስን በቫቲካን አቀባበል አድርገውላቸዋል። በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የተደረገውን የአንድነት የጋራ ውይይት ሂደት አድንቀው፥ ሲኖዶሳዊነት እና የክርስቲያኖች አንድነት ለጠንካራ ክርስቲያናዊ ምስክርነት አስፈላጊ መሆናቸውንም ደግመው ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ለወንጌል ተልዕኮ ከሄደባት ሕንድ ለመጀመሪያ ጊዜ በቫቲካን ታሪካዊ ጉብኝት ካደረገው የማላንካራ ማር ቶማ የሶርያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ሰኞ ኅዳር 1/2017 ዓ. ም. ተገናኝተው ባደረጉት ንግግር ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በሕንድ ከምትገኝ ጥንታዊት የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ጋር መልካም ግንኙነት እንዳላት አረጋግጠዋል።

በሕንድ የምትገኝ የማር ቶማ የሶርያ ቤተ ክርስቲያን ከቶዝሂዮር የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ጋር ኅብረት ያላት ሲሆን ከጥንታዊት ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ ከዩትሬክት ኅብረት እና እንዲሁም ከደቡብ ሕንድ ቤተ ክርስቲያን (ሲኤስአይ) ጋር ያላትን አንድነት ጠብቃ መቆየቷ ይታወቃል። ከዚህም በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሶርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ ከሌሎች የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ጋር የአንድነት ውይይቶችን በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ታውቋል።

የማር ቶማ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት (WCC)፣ የእስያ የክርስቲያን ጉባኤ (CCA) እና በቤተ ክርስቲያን የማኅበራዊ ድጋፍ ተግባርን (CASA)ን ጨምሮ በታዋቂው የክርስቲያኖች አንድነት የጋራ ውይይት ላይ በንቃት የምትሳተፍ ሲሆን ዛሬ በዓለም ዙሪያ ወደ 2.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ምዕመናን እንዳሏት እና አብዛኛዎቹ ዋና መንበሯ በሚገኝበት በሕንድ ኬራላ ግዛት ውስጥ እንደሚኖሩ ታውቋል።

በምሥራቁ እና በምዕራቡ መካከል ድልድይ የሆነች ቤተ ክርስቲያን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለቅዱስ ሲኖዶሱ አቀባበል ካደረጉላቸው በኋላ ባደረጉት ንግግር ለሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቴዎዶስዩስ ማር ቶማ እና ለማላንካራ ምእመናን በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበው የምሥራቁን እና የምዕራቡን ዓለም አብያተ ክርስቲያናትን በማስተሳሰር ላደረጉት የአስተዋይነት ሚና አድናቆታቸውን ገልጸው፥ ቤተ ክርስቲያናቸው ራሱን “በምሥራቁ እና በምዕራቡ ዓለም መካከል የሚገኝ ድልድይ ቤተ ክርስቲያን” በማለት በትክክል እንደሚገልጽ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለፉት አሥርት ዓመታት በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ማለትም በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና በማላንካራ ማር ቶማ የሶርያ ቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ዕድገት በማጤን የማር ቶማ ቤተ ክርስቲያን የተካፈለችበትን ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2022 በሕንድ ኬረላ ግዛት የተጀመሩ እና በሂደት ላይ ያሉ የቅርብ ጊዜ ይፋዊ የጋራ ውይይት ክንውኖችን ጠቅሰው፥ ደረጃ በደረጃ የሚካሄድ ይህ ውይይት አንድ ቀን ቅዱስ ቁርባንን በጋራ ወደ መካፈል እንደሚመራ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

በማቴ. 8:11 ላይ “እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ከምሥራቅ እና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ ከአብርሃም፣ ከይስሐቅ እና ከያዕቆብ ጋርም በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ” ተብሎ የተጻፈውን የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ለመንፈስ ቅዱስ አደራ በሰጡት የጋራ ውይይት መደሰታቸውን ተናግረው የኢየሱስ ክርስቶስን ስጋ እና ደም ከአንድ መንበረ ታቦት የምንካፈልበትን ቀን ቅርብ እንደሚሆን ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የክርስቲያኖች አንድነት እና ሲኖዶሳዊነት
በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን የትብብር ዋና ዋና ርዕሠ ጉዳዮችን ማለትም ሲኖዶሳዊነትን እና የወንጌል ተልዕኮን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀጥለውም፥ ሲኖዶሳዊነት የማር ቶማ ቤተ ክርስቲያን ዋና አካል እና ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በቅርቡ ካካሄደችው የሲኖዶሳዊነት ጉባኤ ጋርም የሚጣጣም መሆኑን ተናግረዋል።

ቅዱስነታቸው በሲኖዶሱ ጉባኤ ላይ ከተገለጹት ጽኑ እምነቶች መካከል አንዱ እና በመጨረሻው ሠነድ ላይ እንደተገለጸው፥ ሲኖዶሳዊነት ከሥነ-ምግባር ፈጽሞ የማይነጣጠል መሆኑን አስታውሰው፥ ሁለቱም ቤተ ክርስቲያናት የተቀበሉት አንድ ጥምቀት እንደሆነ እና ክርስቲያኖች በሙሉ በእምነት እና በታማኝነት ስሜት የሚካፈሉት ይህንኑ ጥምቀት መሆኑን አስረድተዋል።

በጀርመን የጴርጋሞን ከተማ ሊቀ ጳጳስ የነበሩትን እና በ20ኛው እና በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከነበሩት ተደማጭነት ከነበራቸው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት ሊቃውንት መካከል አንዱ፣ ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ ዚዚዮላስን በመጥቀስ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የክርስቲያኖች አንድነት ወደ ፊት ሙሉ በሙሉ እውን የሚሆን ቢሆንም አሁን ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳካት ጸሎትን እና አብሮ መሥራትን የሚጠይቅ መሆኑን አስታውሰዋል።

የክርስቲያኖች አንድነት እና የወንጌል ተልዕኮ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተልዕኮን በማስመልከት እንደተናገሩት፥ ሲኖዶሳዊነት እና የክርስቲያኖች አንድነት ለጠንካራ ክርስቲያናዊ ምስክርነት አስፈላጊ እንደሆኑ ተናግረው፥ የወንጌል ተልዕኮ የክርስቲያኖች የአንድነት ጉዞ ግብ ብቻ አለመሆኑን በመናገር፥ በቅርቡ የተካሄደው የሲኖዶሳዊነት ጉባኤ እንዳቀረበው፥ አንድ ቀን በስብከተ ወንጌል ላይ የተመሠረተውን የክርስቲያኖች አንድነት ለማክበር ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ “ከሞት ስለተናሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ለመመስከር በአንድነት መሥራታችን ለአንድነት ከሁሉም የተሻለው መንገድ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዚህ ራዕይ ብዙ አስተዋፅዖ የምታበረክት የማር ቶማ ቤተ ክርስቲያንን ለሚስዮናዊነቷ ምስጋናቸውን አቅርበው፥ በስብሰባው ላይ የተገኙትን በሙሉ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ!” ጸሎትን በኅብረት እንዲጸልዩ በመጋበዝ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

12 November 2024, 16:30