ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጣሊያን ፍሮሲኖኔ ባደረጉት ጉብኝት የቀረቡ ምስክርነቶችን ሲያዳምጡ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጣሊያን ፍሮሲኖኔ ባደረጉት ጉብኝት የቀረቡ ምስክርነቶችን ሲያዳምጡ  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “እምነት ሰዎችን የሚያደነዝዝ ሳይሆን መገናኛ እና አገልግሎት ነው” ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ 88ኛ የልደት ቀናቸውን ማክሰኞ ታኅሳስ 8/2017 ዓ. ም. አክብረዋል። ይህንን ምክንያት በማድረግ “ላ ሪፑብሊካ” እና “ኢል ኮሪየሬ ዴላ ሴራ” የተሰኙ የጣሊያን ዕለታዊ ጋዜጦች፣ እንዲሁም “ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ” የተሰኘው የአሜሪካ ዕለታዊ ጋዜጣ አንዳንድ የተወሰኑ ቅድመ ዕይታዎችን አሳትመዋል። ጋዜጦቹ ያወጧቸው ጽሑፎች የቅዱስነታቸውን የሕይወት ታሪክ የያዙ እና በጥር ወር ሊታተም ከታቀደው “ስፔራ” በሚል አርዕስት ከተጻፈ የግለታሪክ መጽሐፍ አስቀድሞ የወጡ ጽሑፎች እንደሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጽሐፋቸው ውስጥ በትውልድ አገራቸው አርጄቲና መዲና ቦይነስ አይረስ ውስጥ የነበራቸውን የልጅነት ሕይወት ጭምር አካተዋል። ከዚህ በተጨማሪ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2021 ወደ ኢራቅ ያደረጉትን ታሪካዊ ጉብኝት በማስታወስ፣ ደህንነትን በተመልከተ በጉዞ ወቅት ያጋጠሙ የሎጂስቲክስ ችግሮችን፣ በእምነት እና በቀልድ መካከል ያለውን ግንኙነት በማስመልከትም ጽፈዋል።

በቦይነስ አይረስ ውስጥ በሚገኝ መኖሪያቸው እና ወደ ኢራቅ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ያጋጥማቸውን “የልብ ቁስል” በማስታወስ የጻፉት የግለታሪክ መጽሐፍ ከካርሎ ሙሶ ጋር በመተባበር እንደሆነ ታውቋል። በሞንዳዶሪ አሳታሚ ድርጅት በጥር 6/2017 ዓ. ም. የሚታተመው ይህ መጽሐፍ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ከአንድ መቶ በላይ አገራት ውስጥ እንደሚታተም ታውቋል።

“ላ ሪፑብሊካ” እና “ኢል ኮሪየሬ ዴላ ሴራ” የተሰኙ የጣሊያን ዕለታዊ ጋዜጦች፣ እንዲሁም “ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ” የተሰኘው የአሜሪካ ዕለታዊ ጋዜጣ፥ የቅዱስነታቸውን 88ኛ የልደት ቀናቸውን በማስታወስ፥ አንዳንድ ቅድመ ዕይታዎቻቸውን ታኅሳስ 8/2017 ዓ. ም. ይፋ አድርገዋል።

የቅዱስነታቸው የሠፈር ውስጥ ሕይወት ትዝታዎች
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቦይነስ አይረስ ውስጥ በሚገኝ በፍሎሬስ ባሪዮ ያሳለፉት የልጅነት ሕይወት ልዩ ልዩ ጎሣዎች፣ ሃይማኖቶች እና ባሕሎች የሚገኙበት ውስብስብ ሠፈር እንደነበር ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ “አንድ ሰው የቪሌሮ ጳጳስ እንደሆንኩ ሲነግረኝ ለዚያ ብቁ እንድሆን እጸልይ ነበር” በማለት የልጅነት ጊዜያቸውን አስታውሰዋል። ከካቶሊክ፣ ከአይሁድ እና ከሙስሊም ማኅበረሰብ ጋር ያላቸውን የወዳጅነት ግንኙነት አስመልክተው ሲናገሩ፥ “ልዩነቶች መኖራቸው የተለመደ ቢሆንም፥ እርስ በርስ ተከባብረን እንኖር ነበር” ብለዋል።

“የዘመኑ መግደላዊት”
በቦይነስ አይረስ ውስጥ ያሳለፉትን የልጅነት ልምዳቸውን ያጋሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በመዲናይቱ ጎዳናዎች ላይ የሚቆሙ የሴተኛ አዳሪዎች ሕይወት በማየታቸው የተሰማቸውን ሲናገሩ፥ “ሕይወታቸው የጨለመ እና በጣም አስቸጋሪው የሕልውና ገጽታ ነው” ሲሉ ገልጸውት፥ የጳጳስነት ማዕረግ ከተቀበሉ በኋላ ባሳለፉት የሐዋርያዊ አገልግሎት ዓመታት ውስጥ ሕይወታቸውን ላሻሻሉት አንዳንድ ሴቶች የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ማሳረዳቸውን አስታውሰዋል።

“በአሜሪካ ውስጥም ሴተኛ አዳሪ ሆኜ ሠርቻለሁ፣ ገንዘብም አገኝ ነበር” የምትል ፖሮታን የሚያስታውሷት ቅዱስነታቸው፥ ይህች ሴት ከሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ወጥታ አንድ ካፈቀረችው ሰው ጋር ትዳር መሥርታ መኖር እንደ ጀመረች፣ ባሏ ከሞተ በኋላም በምታገኘው የጡረታ አበል እንደምትተዳደር እና ረዳት የሌላቸው አረጋውያንን እና ራሷንም እየተንከባከበች መኖር እንደ ጀመረች መናገሯን አስታውሰዋል። 

ይህችን ሴት “የዘመኗ መግደላዊት” ሲሉ የገለጿት ቅዱስነታቸው፥ ታማ ሆስፒታል ገብታ እያለች ከመሞቱ በፊት የቅዱስ ቀንዲል ምስጢር ለመቀበል ለመጨረሻ ጊዜ ከሆስፒታል መደወሏን አስታውሰዋል።

በማቴ 21:31 ላይ እንደተገለጸው፥ “በእግዚአብሔር መንግሥት የሚቀድሙን ቀረጥ ሰብሳቢዎች እና አመንዝራዎች” መሆናቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ወ/ሮ ፖሮታ መልካም ሞት እንደ ሞተች እና ዛሬም ቢሆን የሞተችበትን ዕለት በማስታወስ በጸሎት የሚያስቧት መሆኑን በመጽሐፋቸው ጽፈዋል።

ከአባ ፔፔ ጋር ስለነበራቸው ጓደኝነት
በቦይነስ አይረስ ውስጥ በሚገኝ ማረሚያ ቤት የነበሩ ታራሚዎችን እና በካኅናት እጥረት ይቸገሩ የነበሩትን አባ ሆሴ ዴ ፓውላን ወይም አባ ፔፔን በሐዋርያዊ አገልግሎት ይረዷቸው እንደ ነበር አስታውሰዋል።

“ለአርባ ዓመታት ያህል መንግሥት የማያውቀው” እና በአደንዛዥ ዕፅ መበራከት ተስፋ አስቆራጭ የሆኑ ቦታዎችን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ “ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷን ይበልጥ ማጠናከር ያለባት ምእመናን በሚበዙባቸው የከተማ ዳርቻዎች ነው” ብለው፥ “እንደ አባ ፔፔ ያሉ ካህናት በድኅነት በሚሰቃዩት ሰዎች መካከል ወንጌልን በየቀኑ ይመሰክራሉ” ብለዋል።

ሃይማኖት ሰዎችን ማደንዘዣ ሳይሆን በእምነት የሚገናኙበት ነው
ከእነዚህ ጨካኝ እውነታዎች እንደሚመነጭ እውነት ከሆነ ሃይማኖት፥ አንዳንዶች እንደሚሉት ሰዎችን ማደንዘዣ ሳይሆን ግለሰቦችን የሚያጽናና ታሪክ የሚገኝበት ነው” ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አጽንኦት ሰጥተዋል።

“በተቃራኒው ለእምነት እና ለሐዋርያዊ አገልግሎት ምስጋና ይግባቸውና፥ ሰዎች ብዙ ችግሮች ቢያጋጥሟቸውም ሊታሰብ በማይቻል መንገድ መሻሻልን ማሳየት ችለዋል” ብለው፥ “ልክ እንደ እምነት እያንዳንዱ አገልግሎት መገናኘትን የሚፈጥር መሆነ እንዳለበት እና በዚህም በተለይ ከድሆች ብዙ መማር እንችላለን” ብለዋል።

ወደ ኢራቅ የተደረገ ሐዋርያዊ ጉብኝት እና ልብን የሚወጋ "የሞሱል ቀስት"
ከከተማ ዳርቻዎች ድራማ ጀምሮ እስከ ኢራቅ ውድመት ድረስ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እይታ በቆሰለው የሰው ልጅ ላይ ያተኩራል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከየካቲት 5-8/2021 ወደ ኢራቅ ያደረጉትን ታሪካዊ ሐዋርያዊ ጉብኝት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ልብን ስለሚወጋ የሞሱል ቀስት ምንነት ገልጸዋል።

“ሞሱል በዓለም ውስጥ እጅግ ጥንታዊ ከሚባሉ ከተሞች መካከል አንዷ ናት” ሲሉ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ በታሪክና በትውፊት የተሞላች፣ የተለያዩ ሥልጣኔዎች ሲመጡና ሲሄዱ ያየች እና በአንድ አገር ውስጥ አረቦች፣ ኩርዶች፣ አርመኖች፣ ቱርኮች እና ክርስቲያኖች በሰላም አብረው የኖሩባት እንደ ነበር አስታውሰው፥ እስላማዊ መንግሥት ዋና ምሽግ አድርጓት ለሦስት ዓመታት ከተቆጣጠራት በኋላ ወደ ፍርስራሽነት እንደ ተለወጠች መመልከታቸውን ገልጸዋል።

የተመረዙ የጦርነት ፍሬዎች
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በደህንነት ስጋቶች የተባባሰውን የሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን አስቸጋሪ አውድ ሲያስታውሱ፥ “ወደ ማንኛውም ሰው መቅረብ እንደሌለብኝ ምክር ተሰጥቶኝ ነበር” ያሉት ቅዱስነታቸው ነገር ግን የአብርሃም ምድር እንደሆነች በመጥቀስ፥ “የአይሁዶች፣ የክርስቲያኖች እና የሙስሊሞች የጋራ ቅድመ አያት” አገር እንደሆነ መጻፋቸውን ገልጸዋል። 

ሞሱልን በጎበኙበት ወቅት ስለታቀዱት ሁለት የግድያ ሙከራዎች የብሪታንያ የስለላ ድርጅት የሰጠውን ማስጠንቀቂያን የጠቀሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ አንደኛው ፈንጂ የታጠቀች ሴት ስትሆን ሌላኛው ከጭነት መኪና ጋር የተያያዘ እንደ ነበር አስታውሰዋል። ሁለቱም ታጣቂዎች በኢራቅ ፖሊስ ተይዘው መገደላቸው ሲታወስ፥ በዚህም እጅግ ማዘናቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገልጸው፥ “በማከልም የተመረዘ የጦርነት ፍሬ ነበር” ሲሉ ገልጸውታል።

ከግጭት ይልቅ ምክንያቱን ማስቀደም እንደሚገባ የቀረበ ጥሪ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ሁሉ ጥላቻ መካከል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመጋቢት 6/2021 ዓ. ም. ከታላቁ መሪ አያቶላ አሊ አል-ሲስታኒ ጋር በናጃፍ ባደረጉት ስብሰባ፥ “ቅድስት መንበር ለብዙ አሥርተ ዓመታት ጥረት ስታደርግ ቆይታ ባዘጋጀችው ስብሰባ የተስፋ ብርሃንን ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

በአል-ሲስታኒ ቤት ውስጥ በወንድማማችነት መንፈስ የተካሄደው ስብሰባ፣ “በምሥራቁ ዓለም ውስጥ ወዳጅነትን የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናችንን የሚያመለክት በመሆኑ ከመግለጫነት ወይም ከሠነድነት በላይ ነው” ሲሉ ገልጸው፥ “ለነፍሴ ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ እና እንድከበር አድርጎኛል” ሲሉ አስረድተዋል።

ከታላቁ መሪ አያቶላህ ጋር በመሆን “የጦርነት ቋንቋን ትተው ምክንያታዊ እና ጥበብን ማስቀደም እንደሚገባ” ያቀረቡትን የጋራ ጥሪ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “የሰው ልጆች በሃይማኖት ወንድማማቾች ናቸው፣ በአፈጣጠርም እኩል ናቸው” ለሚለው የስብሰባቸው መሪ ርዕሥ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

 

18 December 2024, 15:25