ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የመንፈስ ቅዱስ መልእክተኞች ቀርሜሎሳውያን እህቶችን በቫቲካን ሲቀበሉ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የመንፈስ ቅዱስ መልእክተኞች ቀርሜሎሳውያን እህቶችን በቫቲካን ሲቀበሉ   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ሐሜት ለስብከተ ወንጌልን እንቅፋት እንደሆነ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመንፈስ ቅዱስ መልእክተኞች ቀርሜሎሳውያን እህቶችን በቫቲካን ተቀብለው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ለገዳማውያቱ ባስተላልፉት መልዕክት፥ ባሕላቸውን መሠረት ያደረገ የጸሎት እና የስብከተ ወንጌል ሕይወት እንዲመሩ ጋብዘው፥ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው የመጀመሪያ መልዕክቱ 9:16 “ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ! ያለውንም አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን የተናገሩት መንፈሳዊ ጉዞን በማድረግ ከብራዚል እና ከአንዳንድ የአውሮፓ አገራት ወደ ሮም ለመጡት የመንፈስ ቅዱስ መልእክተኞች ቀርሜሎሳውያን እህቶች ዓርብ ኅዳር 27/2017 ዓ. ም. በሰጡት ማሳሰቢያ እንደ ነበር ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገዳማውያቱ ማኅበራቸው የተመሠረተበትን 40ኛ ዓመት ባከበሩበት ዘንድሮ 4ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ አዲስ የአመራር አባላትን መምረጣቸውን አስታውሰው፥ ዓመቱ ገዳማውያቱ “ለሁሉም ሰው ሊደርስ የሚገባውን የወንጌል አገልግሎት እና የእግዚአብሔርን ቃል ለማስፋፋት በየቀኑ ቁርጠኝነትን እንዲያሳዩ የሚጠይቅ መልካም ማሳሰቢያ ነው” ብለዋል።

አክለውም ሁሉም ክርስቲያኖች ወንጌልን ለዓለም የመስበክ ግዴታ እንዳለባቸው በመግለጽ፥ ገዳማውያቱ ሁል ጊዜ ከሃሜት ፈተና እንዲርቁ በማሳሰብ፥ “ሐሜት ስብከተ ወንጌልን ይቃወማል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ምክንያቱም ወንጌል ሁል ጊዜ በደስታ የሚቀበል ሲሆን፥ ሐሜት ግን ሌሎችን እንድንኮንን ያደርገናል” ብለዋል።

የቀርሜሎሳውያን እህቶች የወንጌል እና የጸሎት ሕይወት የመምራት ልዩ ተልዕኮ እንዳላቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ “በማኅበራችሁ ውስጥ የምታበረክቱት የወንጌል አገልግሎት የሚስዮናዊነት እንቅስቃሴ እና ሌሎች መስኮችም ጥንታዊ እና ውብ ከሆነው የቀርሜሎሳዊ ወግን ከተከተለ የጸሎት እና የማሰላሰል ሕይወት ጋር የተቆራኘ ነው” በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

 

07 December 2024, 15:36